የእስራኤል የስደት ተመላሾች ጉዳይ ሚኒስትር ፕኒና ታምኖ ለስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

70

አዲስ አበባ ህዳር 20/2013 (ኢዜአ) የእስራኤል የስደት ተመላሾች ጉዳይ ሚኒስትር ፕኒና ታምኖ ለስራ ጉብኝት ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገቡ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ እና በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋይል ሞራፍ ቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ሚኒስትሯ ወደተወለዱባት ኢትዮጵያ አገረ-እስራኤልን በመወከል ለስራ ጉብኝት በመምጣታቸው ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ወርሃ መጋቢት በተደረገው አገራዊ ምርጫ ውድድር ማሸነፋቸውን ተከትሎ በአዲስ ገቢ ስደተኞች ሚኒስትርነት የተሾሙት ፕኒና፤ በቀጣይ ቀናት በሚኖራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ በሚገኙ ቤተ እስራኤላዊያን የመመለስ ሂደት በተመለከተ ምክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ለሺህ ዘመናት ታሪካዊ ግንኙነት ባላቸው በኢትዮጵያና እስራኤል የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጉዳዮች ከአገሪቱ የስራ ሃላፊዎች ጋር ይመክራሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ወይዘሮ ፕኒና ታምኖ እሸቴ በእስራኤል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያገኙ የመጀመሪዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም