ቀጥታ፡

በሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19/2013(ኢዜአ) ሕግ በማስበር ዘመቻ ላይ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት 137 ሰንጋዎች፣ 40 በጎችና ፍየሎች እንዲሁም ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተበረከተ። 

ከደቡብና ከኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰበውን ድጋፍ የሕዝቡ ተወካዮች በኢፌዴሪ ምድር ኃይል ተገኝተው አስረክበዋል።

ድጋፉን ካደረጉት መካከል ከደቡብ ክልል የሸካ ዞን ሕዝብ 75 ሰንጋዎችና ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

በዚሁ ክልል የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ሕዝብ 19 በሬዎች፣ ዘጠኝ ፍየሎችና በጎችና 200 ሺህ ብር ለግሷል።

እንዲሁም የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ሰጥተዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የሆምቾ አካባቢ ነዋሪዎች 43 በሬዎችና 31 በጎች አበርክተዋል።

ተወካዮቹ ሕዝቡ ድጋፉን ያደረገው ከሃዲው የህወሓት ጁንታ ቡድን በሰሜን ዕዝ ሠራዊት የፈጸመው ኢ- ሠብዓዊ ድርጊት ስላስቆጣው በእልህና በቁጭት ተነሳስቶ ድጋፉን ማድረጉን ተናግረዋል።

የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አልማው ዘውዴ በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ ሕዝቡ የሚያደርገው ድጋፍ በገንዘብም በዓይነትም እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ሕዝቡ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ድጋፉን የተቀበሉት የመከላከያ ሚኒስቴር ፋይናንስ ስራ አመራር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሲሳይ ሕዝቡ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ ለሠራዊቱ ትልቅ የሞራል ስንቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም