በአማራ ክልል በመኸሩ ወቅት በተለያዩ ሰብል ከለማው መሬት ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ምርት ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በመኸሩ ወቅት በተለያዩ ሰብል ከለማው መሬት ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ምርት ተሰበሰበ
ባህርዳር፣ ህዳር 19 /2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል በመኸሩ ወቅት በተለያየ ሰብል ከለማው መሬት ውስጥ ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ ።
በመንግስት ጥሪ ተደርጎላቸው በህግ ማስከበር ዘመቻው እየተሳተፉ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት በልዩ ትኩረት ሰብላቸው እየተሰበሰበ መሆኑም ተመልክቷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የተሰበሰበው ሰብል በመኸር ወቅት ከለማው አራት ሚሊዮን 200 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ነው።
በደረሰ ሰብል ሰብሰባ ወቅት አርሶ አደሩ 60 የማጨጃና የመውቂያ ኮምባይነሮችን መጠቀሙን ጠቅሰው ይህም የምርት ብክነትን መቀነስ ከማስቻሉ ባሻገር የምርት ጥራቱ እንዲጠበቅ ማገዙን ተናግረዋል።
ከተሰበሰበው ሰብል ውስጥ ገብስ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ሰሊጥ እና ጥራጥሬ እንደሚገኙበት ያስረዱት አቶ ተሰፋሁን
ቀሪውን የሰብል ምርትም እንደደረሰ የሚሰበሰብ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግስት ጥሪ ተደርጎላቸው በህግ ማስከበር ዘመቻው እየተሳተፉ የሚገኙ የሚሊሽያና የልዩ ኃይል አባላት ሰብልም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ የሰበሰበውን ምርት ፈጥኖ በመውቃት ምርቱን ወደ ጎተራ እንዲያስገባ አሳስበዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረኤልያስ ወረዳ የጓይ ቀበሌ አርሶ አደር እንዳላማው ቢሻው በሰጡት አስተያየት ሶስት ሄክታር ተኩል መሬታቸውን በስንዴ፣ ጤፍ፣ ቆሎና ዳጉሳ ሰብል በማልማት እንክብካቤ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
እስካሁንም በአንድ ሄክታር መሬት ላይ የደረሰውን የስንዴና ጤፍ ሰብል በሰው ጉልበትና ኮምባይነር አጭደውና ወቅተው መሰብሰባቸውን ጠቁመው፤ ቀሪውንም ለመሰብሰብ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በክረምት ካለሙት 2 ሄክታር መሬት ቀድሞ የደረሰውን የቢራ ገብስና ባቄላ ሰብል መሰብሰባቸውን የገለጹት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ የዱርጌ ማሽንት ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃን ይመር ናቸው።
በመኸሩ ወቅት በአማራ ክልል በተለያየ የሰብል ዘር ከለማው መሬት ከ127 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።