ቀጥታ፡

የቤተ-ክርስቲያኗ የሰንበት ተማሪዎችና ምዕመናን ደም ለገሱ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የኮተቤ ደብረ ልዑል ዳግማዊ ቁልቢ ቅዱስ ገብርዔል ቤተ-ክርስቲያን የሰንበት ተማሪዎች፣ የሰንበት ተማሪዎች ማኅበር አባላትና ምዕመናን ደም ለገሱ፡፡

''ደሜን ለወገኔ!'' መርሐ ግብር በትራፊክ አደጋ፣ በወሊድና በሌሎች ምክንያቶች ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ደም ለማሰባሰብ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች የሚለግሱት ደም የሌሎችን ሕይወት የሚታደግ በመሆኑ ደስታ እንደሚሰማቸው ተናግረው፤ “መነቃቃት እየታየበት ያለውን የደም ልገሳ በጎ ተግባር ቀጣይነት ያለው ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ለዚህም የደም ባንክ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርና የጤና ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የፍቅረ ሰላም ዘኮተቤ መንፈሳዊ አባላት መካነ ሠላም የሰንበት ትምህርት ቤት አስተባባሪ ሊቀ ትጉሃን ዲያቆን ፋሲል ገብረሚካኤል ደሙን የሌሎችን ሕይወት ለማትረፍ ሲለግስ ደስታ እንደተሰማው ገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ቀደም ሲል 180 ያህል ሰዎች ደም እንደለገሱ ተናግሯል፡፡

በቤተ ክርስቲያኗ ከ500 በላይ በጎ ፈቃደኞች ደም ለመለገስ መዘጋጀታቸውንም ገልጿል።

የማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ወልዱ “መርሃ ግብሩ በዘላቂነት ደም የሚለገስበት እንዲሆን ጥረት ይደረጋል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም