በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በተሳሳተ መንገድ የመረዳት ዝንባሌ እንዳለ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በተሳሳተ መንገድ የመረዳት ዝንባሌ እንዳለ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 19/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በተሳሳተ መንገድ የመረዳት ዝንባሌ መኖሩን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣራት አመለከተ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣራት እንዳመለከተው፤ አራት ጉዳዮችን በተሳሳተ መንገድ የመረዳት ዝንባሌ አለ።
በተሳሳተ መንገድ እየተገለጹ ያሉት ጉዳዮች ኢትዮጵያ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እየገባች ነው የሚል ማምታታት አንዱ መሆኑን የገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣራት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የትግራይ ከተሞችን እየደበደበ ነው፣ ሰራዊቱ መቀሌን በአየር እየደበደበ ነው የሚል እና ‘ኢትዮጵያ ለመቀሌ ከተማ ምህረት የለም’ ብላለች የሚሉ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች እየተንጸባረቁ እንደሆነ አመልክቷል።
ዘመቻው ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የሚከታት ሳይሆን ከዚያ የሚታደጋት እንደሆነ ገልጾ፤ ዘመቻው ግልጽ፣ የተገደበና የሚፈጸም ዓላማ እንዳለው ጠቁሟል።
ዘመቻው ያስፈለገው የታጠቁትን የህወሃት ጁንታ ለህግ ማቅረብ ዋና ዓላማው መሆኑን ገልጾ፤ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅም አመልክቷል።
የመከላከያ ሰራዊቱ በሚያካሂደው ዘመቻ በከተሞች ውጊያ እንደማያካሂድ የገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣራት፤ ከህወሃት ጁንታ ታጣቂዎች ጋር በሚዋጋበት ወቅት ጭምር በንጹሃን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።
እስካሁን ባለው ጊዜም መከላከያ ሰራዊቱ ለንጹሃን የሚያደርገውን ጥንቃቄ እንዳሳካ ተገልጿል።
የህወሃት ቡድን የአገር መከላከያ ሰራዊቱ የአየር ጥቃት በከተሞች እንደፈጸመና ንጹሃን እንደተጎዱ በመግለጽ በርካታ የተፈበረኩ ውንጀላዎችን እንዳቀረበ አስታውሶ፤ የሰራዊቱ የአየር ጥቃት እየተፈጸመ ያለው በተለዩ ወታደራዊ ዲፖዎችና መሳሪያ በተከማቹባቸው ኢላማዎች ላይ መሆኑን ጠቅሷል።
በሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶችና መኖሪያ አካባቢዎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቅሷል።
መንግስት ንጹሃንን ኢላማ ያደረገ ዘመቻ እንደማያካሂድ በተደጋጋሚ መግለጹን ያስታወሰው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣራት፤ በአንድ ኮሎኔል የተሰጠ መግለጫ ከአውዱ ውጪ የሆነ ትርጉም ተሰጥቶት የኢትዮጵያን መንግስት ለመወንጀል ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ አመልክቷል።
በመቀሌ ዘመቻ ለማካሄድ የጁንታውን ቡድን አባላት በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ በመንግስት የ72 ሰዓት ጊዜ እንደተሰጣቸው አስታውሶ፤ መንግስት የዘመቻውን የመጨረሻ ምዕራፍ ለማካሄድ መዘጋጀቱን ማስታወቁን ገልጿል።
በወታደራዊ ደህንነት በኩል በተገኘው መረጃ ከዚህ በተጻጻሪ የህወሃት ቡድን በንጹሃን ላይ ጭፍጨፋ ለመፈጸም መዘጋጀቱ እንደተደረሰበት ገልጾ፤ ቡድኑ በሃሰት ፕሮፓጋንዳው እያታለለ መንግስት በሚያካሂደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የዓለም ዓቀፍ ማህበረሰቡ ጣልቃ እንዲገባ እየሞከረ እንደሆነ አመልክቷል።