ቀጥታ፡

የጋምቤላ ህዝብ አንድነቱን አጠናክሮ የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ በጋራ ሊሰራ ይገባል-ምክር ቤቱ

ጋምቤላ፣ ህዳር 19/2013(ኢዜአ) የጋምቤላ ክልል ነዋሪ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር የአካባቢውን ሠላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ አቶ ጁል ናንጋል አሳሰቡ ።

’’እኩልነትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና’’ መሪ ሀሳብ 15ኛው የኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ባተኮሩ ውይይቶችና ደም ልገሳ መከበሩ እንደቀጠለ ነው።

የምክር ቤቱ አፈ- ጉባኤ በጋምቤላ ከተማ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ’’የህወሓት ጁንታ ባለፉት 27 ዓመታት በክልሉ ሲፈጽማቸው የነበሩት የጭቆናና ዘረፋ እኩይ ተግባራት አልበቃው ብሎ አሁንም በተላላኪዎቹ ተጨማሪ ጥፋቶችን ለማድረስ አልቦዘነም ’’ ብለዋል።

በተለይም የሀገር ጋሻና መከታ በሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት መቼውንም ቢሆን በኢትዮጵያ ህዝቦች የማይዘነጋ እኩይ ተግባር መሆኑን አውስተዋል።

ህዝቡ ቀደም ሲል በህወሓት ጁንታ ሲሰበክ የነበረውን ከፋፋይ አስተሳሰቦችን በማስወገድ አንድነቱን አጠናክሮ የአካባቢውን ሠላም ነቅቶ ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ህግን ለማስከበር ለተጀመረው ዘመቻ ስኬትም የክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ጀምስ ዴንግ በሰጡት አስተያየት ጁንታው ህወሓት ባለፉት 27 ዓመታት ሲፈጽማቸው የነበሩት የጭቆና የሌብነት ተግባራት ሲቋረጡበት ሀገር ለማፍረስ እየጣረ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ሀገርን ለማዳን በጁንታው ላይ የጀመረውን ህግ የማስከበር ዘመቻ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ጁንታው በክልሉ ባለፉት ዓመታት በርካታ የከተማና ገጠር መሬትን ለባንክ በማስያዝ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ዘርፎ መሰወሩን የገለጹት ደግሞ ሌለው ተሳታፊ አቶ ወረቲ አሰፋ ናቸው።

ይህ ግፍና በደል አልበቃው ብሎ አሁንም አሰቃቂና አረመኔያዊ ድርጊት እየፈጸመ ነው ያሉት አቶ ወረቲ በቡድኑ ላይ የተጀመረው ህግ የማስከበር ተግባር በማያዳግም መልኩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልል ደረጃ እየተከበረ ያለው 15ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል እስከ ህዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ እንደሚቆይ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም