ቀጥታ፡

ምርት ገበያው ለግብርና ምርት አቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች ልዩ የግብይት መስኮት ከፈተ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለግብርና ምርት አቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች ልዩ የግብይት መስኮት መክፈቱን አስታወቀ፡፡

ዥንጉርጉር ቦሎቄና ነጭ የርግብ አተር ወደ ዘመናዊ ግብይቱ ተቀላቅለዋል፡፡

ልዩ መስኮቱ ኢንዱስትሪዎቹ የጥራት ደረጃው በላቦራቶሪ የተረጋገጠ አኩሪ አተር በኤሌክትሮኒክ የግብይት ሥርዓት አማካይነት የሚገዙበት ነው።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተመዝግበው እውቅና የተሰጣቸው 16 አቀነባባሪዎች ወደ ግብይት ሥርዓቱ እንዲገቡ መደረጉን ምርት ገበያው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የልዩ መስኮት አገልግሎቱ ኢንዱስትሪዎቹ በግብይት ሥርዓቱ ሕጋዊ አሠራርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ስልጠና ተሰጥቷቸው በኤሌክትሮኒክ የግብይት መድረክ አማካይነት መግዛት የሚችሉበት አሠራር መፍጠሩን ገልጿል፡፡

በቅርቡም ተጨማሪ ኢንዱስትሪዎች ወደ ልዩ የግብይት መስኮት ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል ብሏል።

የግብይት ስርዓቱን የተቀላቀሉ የዥንጉርጉር ቦሎቄና ነጭ የርግብ አተር ግብይት በይፋ ተጀምሯል፡፡

የምርቶቹ ግብይት በምርት ገበያ በኩል መካሄዱ ምርቱ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ፣ አርሶ አደሩ በቂ የገበያ መረጃ በማግኘት የመደራደር አቅሙን እንዲያሳድግና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ወደ ገበያ ለማስገባት እንደሚያስችለውም አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ለምርቶቹ ተስማሚ ሥነ ምህዳሮች ስላሏት በየዓመቱ ዥንጉርጉር ቦሎቄ ወይም ፒንቶቢን ከ435 ሺህ ኩንታል በላይ፤ ነጭ የርግብ አተር ደግሞ ከ120 ሺህ ኩንታል በላይ እንደሚመረቱ አስታውቋል።

ከዚህ ውስጥ ዥንጉርጉር ቦሎቄ 70 በመቶ፤ ነጭ የርግብ አተር 90 በመቶ ከቤተሰብ ፍጆታ አልፈው ለገበያ ይቀርባሉ፤ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ኬንያና ታንዛንያም ዋነኞቹ ገዢዎች ናቸው።

ምርት ገበያው የሚያገበያያቸው ምርቶች ብዛት ወደ 12 መድረሱንም አመልክቷል።

በተለይ ዥንጉርጉር ቦሎቄ ጥቅል ስያሜ ሆኖ በሥሩ ቀይ በነጭ፣ ነጭ በግራጫ፣ ክሬም በቀይና ነጭ በቀይ እንዲሁም ክሬማማ፣ ቢጫና ጥቁር ቦሎቄዎችን ያጠቃልላል።

ምርት ገበያው የሚጠበቅበትን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣትና ደንበኞቹን ለማገልገል አዳዲስ አሰራሮችን በመቀየስና በማሻሻል ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል።

በዚህ ዓመት በቡሌ ሆራና በመቱ የተገነቡት ሁለት መጋዘኖች እንዲሁም በጎንደር፣ በአዳማና በጅማ የተገነቡ የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት ሥራ እንደሚጀምሩም ገልጿል።

በተጨማሪም በሚዛንና በቴፒ ሁለት ተጨማሪ ቅርንጫፎች ይከፈታሉ ብሏል።

አዲስ በሚከፈቱትና አሁንም በሥራ ላይ ባሉት የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት አርሶ አደሮችና አቅራቢዎች የምርት ገበያው አባል ሳይሆኑ ምርታቸውን በቀጥታ መሸጥ የሚችሉበት አሠራር ሥራ ላይ እንደሚያውል አመልክቷል።

ምርት ገበያው በዚህ በጀት ዓመት 784 ሺህ ቶን ምርት ለማገበያየት ያቀደ ሲሆን ባለፉት አራት ወራት 142 ሺህ ቶን ምርት በ9 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር አገበያይቷል።

ከሕዳር ጀምሮ ያለው ወቅት ምርት ተሰብስቦ ወደ ገበያ የሚቀርብበት በመሆኑ ከፍተኛ ምርት ይገበያያል ተብሎ እንደሚጠበቅም ምርት ገበያው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም