መርማሪ ቦርዱ የመጀመሪያውን ዙር የመስክ ምልከታ እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መርማሪ ቦርዱ የመጀመሪያውን ዙር የመስክ ምልከታ እያካሄደ ነው
ህዳር 19/2013 ዓ.ም (ኢዜአ) ሕገ-መንግስቱንና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል በቅርቡ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ የመጀመሪያውን ዙር የመስክ ምልከታ በማካሄድ ላይ ነው፡፡
ቦርዱ ህዳር 14 ቀን 2013 ዓ.ም የጀመረው የመስክ ምልከታ እስካሁን በባህርዳር፣ በጎንደርና በዳንሻ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የምርመራ ስራውን አከናውኗል፡፡
የመርማሪ ቦርዱ አባላት የጽንፈኛው ቡድን በአየር መንገዶቹ አካባቢ ያስወነጨፈባቸውን ቦታዎች ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፤ የባህርዳር አየር ማረፊያ የስራ ኃላፊዎች ለመርማሪ ቦርዱ አባላት በአየር ማረፍያው አካባቢ የደረሰውን ጉዳት ባስጎበኙበት ወቅት ስለ ክስተቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የጉዳቱ ሙሉ መረጃ በባለሙያዎች ተጠንቶ ይፋ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
የመርማሪ ቦርዱ አባላት በሲቪል አየር ማረፍያ የተደረገው የጥቃት ሙከራ ኢሰብዓዊ መሆኑን ገልጸው፤ ምናልባት ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈጸም ስለሚችል ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ለሁለቱም አየር ማረፊያ የስራ ኃላፊዎች ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
የመርማሪ ቦርዱ አባላት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታልን በጎበኙበት ወቅት በከሃዲው የህወሃት ቡድን አስገዳጅነት በተሰማሩበት ግጭት የተጎዱ ታካሚዎችን ተመልክተዋል፡፡
አባላቱ በሆስፒታሉ የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው የነበሩ የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላትን ባነጋገሩበት ወቅት ታካሚዎቹ ተገቢ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እያካሄደ ባለው ህግ የማስከበር ዘመቻ እጃቸውን ለመከላከያ ሰራዊት የሰጡት እንዲሁም ቆስለው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው የሚገኙት የህወሃት ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል በህወሃት አመራሮች ከተነገራቸው ማስፈራሪያ በእጅጉ የሚቃረን እርዳታና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በዘመቻው የተጎዱ ታካሚዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።
የሆስፒታሉ የስራ ሃላፊዎች የህክምና ቁሳቁስና የበጀት እጥረት በሆስፒታሉ መኖሩን ለሚመለከታቸው የበላይ አካላት በመግለጽ ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን ለመርማሪ ቦርዱ አስረድተዋል፡፡
የመርማሪ ቦርዱ አባላት በበኩላቸው በሆስፒታሉ ለታካሚዎቹ እየተደረገ ያለው የህክምና እርዳታ በጣም ጥሩ መሆኑን ገልጸው፤ ባጠቃላይ የሆስፒታሉን ባለሙያዎችና ሰራተኞች ከመደበኛ ስራቸው በላይ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ ወጣቶችና ባለሀብቶች ሀገራዊ በሆነ ስሜት ድጋፍ እየሰጡ በመሆኑ አመስግነዋል፡፡
በቀጣይም የሆስፒታሉን አቅም ለመገንባትና ለገጠመው የበጀትና የህክምና ቁሳቁስ ጉድለት መፍትሄ ለማፈላለግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንደሚሰሩ የመርማሪ ቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ ጠቁመዋል፡፡
መርማሪ ቦርዱ ወደ ዳንሻ ባመራበት ወቅት በህወሃት ጁንታ የመጀመሪያው የጥቃት ሰለባ የሆነውን የሰሜን እዝ 5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የጎበኙ ሲሆን ከሃዲው ቡድን በክፍለ ጦሩ ያደረሰውን ጥቃት በተመለከተ ለመርማሪ ቦርዱ አባላት ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በወቅቱ ከተቃጣባቸው ጥቃት ሶስት ቀንና ለሊት ሙሉ በከፍተኛ ጀብደኝነት ጥቃቱን መክተው ለድል የበቁት የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ሙሉአለም አድማሱ መርማሪ ቦርዱ በአካል ተገኝቶ ስለ ጥቃቱ መረጃ መሰብሰቡን አድንቀዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደርጉት የሞራል ድጋፍ ሰራዊቱን በእጅጉ እንደሚያበረታታውም ገልጸዋል፡፡
የመርማሪ ቦርዱ አባላት በጥቃቱ ክፉኛ ማዘናቸውን ገልጸው፤ ለህይወታቸው ሳይሳሱ በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜትና ተጋድሎ ሀገሪቱን ከመበታተን አደጋ በማዳናቸው ጀኔራሉንና የክፍለ ጦሩን አባላት በጠቅላላ አመስግነዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድ የመስክ ምልከታውን የቀጠለ ሲሆን፤ በቀጣዮቹ ቀናት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ መረጃዎቹን ይሰበስባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘው መረጃ ያሳያል።