የዲያስፖራውን የልማት ተሳትፎ ለማጎልበት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲያስፖራውን የልማት ተሳትፎ ለማጎልበት እየተሰራ ነው
አዳማ ህዳር 18/2013 (ኢዜአ) የዲያስፖራውን የልማትና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማጎልበት እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጄንሲ ገለጸ።
ኤጄንሲው ዲያስፖራው ቀጣይ በሀገር ልማት ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ ከባላድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት የሚቆይ የምክክር መድረክ ዛሬ ጀምሯል።
የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሠላማዊት ዳዊት በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በተለይ በባንክ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ጨምሮ በሌሎች የሀገር ልማቶች የዲያስፖራው ተሳትፎ እንዲጎልበት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ውጤታማ ስራ ተከናውናል።
በእነዚህ ዘርፎች የዲያስፖራ ተሳትፎ ለማጎልበት የሚካሄዱትን ስራ መቀጠላቸውን አሰረድተዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መብት የማስከበር በተለይ የስራ ፈቃድና ምዝገባ፣ በውጭ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ተፈተው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ከመንግስት ጋር ሆነው በርካታ ስራ ማከናወናቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ በተለያየ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ከውጭ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን በቀጥታ የማገዝ፣ መደገፍና ክትትል ማድረግ ላይ የነበረውን ክፍተት ማረም መቻሉንም አስረድተዋል።
በዚህም ዲያስፖራው ይዘው የሚመጡ ፕሮጄክቶችን አዋጭነት፣ የፋይናንስ አቅማቸውና የጠቅላላ ካፒታላቸውን 25 በመቶ በውጭ ምንዛሪ በባንክ ማስገባታቸውን በማረጋገጥ ፈጥነው እንዲስተናገዱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሎች የልማት ፕሮጀክቶች ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገባቡ ከማድረግ አንፃር አሁንም ክፍተት አለ ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ ፕሮጀክቶቹ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ በዘላቂነት ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰሩ አመልክተዋል።
የዲያስፖራውን የውጭ ምንዛሪ ፍሰት ለማሳደግ አምናና በተያዘው የስራ ዘመን የመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት ከ4 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን ዶላር በላይ በቀጥታ በባንክ ወደ ሀገር ወስጥ መላኩን የገለጹት ደግሞ በኤጀንሲው የእቅድ ዝግጅትና ክትትል ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ደሜ ናቸው።
በተጨማሪም ከ14ሺህ በላይ የዲያስፖራ አባላት የውጭ ምንዛሪ ማስቀመጫ የሂሳብ ደብተር በመክፈት ከ21 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ በሀገር ውስጥ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የዲያስፖራን የልማት፣ ኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም ተሳትፎ ለማጎልበት በተደረገው ጥረት ከ2ሺህ በላይ ዲያስፖራ በተለያዩ 33 ፕሮጀክቶች እንዲሰማሩ መደረጉንም አስረድተዋል።
ለልማት በተደረገው ሀገራዊ ጥሪ ዲያስፖራው ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ለገበታ ለሀገር ድጋፍ ያደረገ ማድረጉን ጠቅሰው ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ በተያዘው የስራ ዘመን የመጀመሪያ ሩብ የበጀት ዓመት ብቻ ከዲያስፖራው ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
በቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር፣ በጤናና ደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ ከባለደርሻ አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኮሮናን ለመከላከል መንግስት ባደረገው ጥሪ መሰረትም ባለፉት ስምንት ወራት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና ዓይነት ከዲያስፖራው ድጋፍ መገኘቱን አመልክተዋል።