ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል
አዲስ አበባ ህዳር 18/2013 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ቀን ከህዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዝግጀቶች እንደሚከበር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን ቀኑን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
ቀኑ ''ለሰብአዊ መብቶች መከበር እንትጋ'' በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ ለ14ኛ ጊዜ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ72ኛ ጊዜ እንደሚከበር ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አማካሪ አቶ አሮን ማሾ እንዳሉት ቀኑ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ የጸደቀበትን ቀን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
በዓሉ በሚከበርባቸው ቀናትም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ጽህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጥምረትና ሌሎችም ሰብአዊ መብት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ገለልተኛ ድርጅቶች በጋራና በተናጠል የተለያዩ ዝግጅቶችን እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል።
ከህዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ቀኑ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የጠቆሙት አማካሪው፣ ለዚህም በዓበይት የሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በበይነ መረብ የሚካሄ የፓናል ውይይቶችን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በሚካሄደው የበዓሉ ማጠናቀቂያ ሥነ ስርአት ላይ ሁሉም ድርጅቶች በጋራ በተገኙበት የኢትዮጵያን የሚያንጸባርቅ የፎቶ አውደ ርዕይና የመድረክ ትዕይንቶች ይካሄዳሉ።
"በተጨማሪም ፆታዊ ጥቃትን ለማስቀረት የተደረገውን የ16 ቀን የህብረተሰብ ንቅናቄ የተመለከተ የስዕል ትእይንት ይቀርባል" ብለዋል።
የቀኑ መከበር የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ ለሰብአዊ መብት ጥሰት የተጋለጡ ዜጎች መፍትሄ እንዲያገኙ ለመጠየቅ ተጨማሪ ዕድል ይሰጣልም ብለዋል።
የግጭት አፈታትና መከላከል ስርአቶች በሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ፣ ሁሉንም ወገኖች ያሳተፉና ግልጽነት የተሞላባቸው እንዲሆኑ ጥሪ ይደረጋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሰአብአዊ መብት ድርጅቶች ሕብረት ዳይሬክተር መስዑድ ገበየሁ፤ ሰብአዊ መብት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስትም ለአሰራር ማነቆ የሆኑ ህጎችን በማንሳት እና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ድርጅቶቹ ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማድረግ አለበት ብለዋል።
በኢትዮጵያ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ኮሚቴ መቋቋሙንም ገልጸዋል።