ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማቾች ማህበርና የቡርጂ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ ህዳር 18/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማቾች ማህበር አባላት በጡረታ ከሚያገኙት ገንዘብ በማዋጣት ለአገር መከላከያ ሰራዊት የ100 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉን የማህበሩ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ በምድር ሃይል ተገኝተው አስረክበዋል።

በሰራዊቱ ላይ በህወሃት ጁንታ የተፈጸመው ክህደት እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

“ከአገራችን ኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች አገሮች ሰላም መስዋዕትነት በሚከፍለው የአገር መከላከያ ሰራዊት የአገር ኩራት እንጂ ክህደት ሊፈፀምበት አይገባም ነበር” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰራዊት ጠንካራ ስነልቦና እና ጀግንነት ያለው በመሆኑ ሁሉንም ነገሮች አልፎ አሁን ላይ የአገሪቷን ሀልውና ማስጠበቁ እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ የኮሪያ ዘማቾች ማህበር አባላት ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

የማህበሩ ድጋፍ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑንም ገልጸዋል።

ሰራዊቱ የአገር አንድነትን አስጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ የማስረከብ ሃላፊነቱን በብቃት እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።

በተያያዘ ዜና በደቡብ ክልል የቡርጂ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ለሰራዊቱ 165 ኩንታል ጤፍ በምድር ሃይል በመገኘት አስረክበዋል።

ድጋፉን ያስረከቡት ከልዩ ወረዳው የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎችና የልዩ ወረዳው አስተዳዳሪዎች ናቸው።

የቡርጂ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከድር አደም፤ የአገር አለኝታ በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጁንታው ያደረሰው ጥቃት እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

የልዩ ወረዳው ህዝብና አስተዳደር ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጎን መሰለፉን ለማረጋገጥ አካባቢው ይበልጥ የሚታወቅበትን የጤፍ ምርት በተወካዮቹ በኩል መበርከቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም  ድጋፎችን ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ የሚኒስትር ዴኤታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ጌታቸው ሲሳይ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም