ኢትዮጵያዊነት ከተራ ዲስኩር፣ ከእንጭጭ ዘረኝነት፣ከስሜታዊ ቁጣና ከደመነፍሳዊ ሩጫ በላይ ነው-አቶ ነብዩ ስሁል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊነት ከተራ ዲስኩር፣ ከእንጭጭ ዘረኝነት፣ከስሜታዊ ቁጣና ከደመነፍሳዊ ሩጫ በላይ ነው-አቶ ነብዩ ስሁል
ህዳር 18/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ፣ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ አገረ-መንግስት ግንባታ ከተራ ዲስኩር፣ ከእንጭጭ ዘረኝነት፣ ከስሜታዊ ቁጣና ከደመነፍሳዊ ሩጫ በላይ ነው ሲሉ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ገለፁ።
አቶ ነብዩ ለሀገሪቱ የሚጠቅም አጀንዳና ራእይ የሌላቸው አፍራሽ ሃይሎች ሁሉ ከህግ በታች መሆናቸው የሚረጋገጥበት ግዜ ቅርብ ነው ብለዋል።
አቶ ነብዩ መንግስት የጀመረው ህግ የማስከበር ስራም አንድ ቦታ ላይ የሚቆም አለመሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ህወሓት በቀደደለት ቦይ እየፈሰሰ ለህወሓት ተግባር ልታገል የሚል ማንኛውም አካል ለሀገር እና ለተጀመረው የለውጥ አጀንዳ ከህወሓት ባልተናነሰ ደረጃ ጋሬጣ ነው ብለዋል።
የፓርቲው ፅህፈት ቤት ሀላፊ ጠንካራዋን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በአንድነት፣ በመተሳሰብና በወንድማማችነት ወደ መጪው ግዜ መሻገር እንደሚገባ ገልፀዋል።
በቅርቡ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ነብዩ ስሁል የህወሃት ቡድን ህዝብን በመከፋፈል ፤ሰዎችን በማጥቃትና ተገዳዳሪ ሃሳብን ሲጨፈልቅ እንደነበር ተናግረዋል።
የህወሃት አገዛዝ በኢትዮጵያ ያለውን የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ግንባታ የሚያደናቅፍ ቡድን እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።