ቀጥታ፡

የህወሃት ትግል ራስን ለማስተዳደር ሳይሆን ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር ነው- ፎሬይን ፖሊሲ

 የትግራይ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ ሰሜን እዝ በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ

መንግስት ህግ የማስከበርና አገር የማዳን እርምጃ መውሰድ ከጀመረ ከሁለት ሳምንት በላይ ሆኗል። የመንግስትን ህግ የማስከበር ተልእኮ ተከትሎ የአገራት መሪዎች፣ የዓለም መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የፖለቲካ ተንታኞች እንደየአረዳዳቸው በተለያየ መልኩ ገለጻዎችንና  ትንታኔዎችን  እየሰጡ ይገኛል።

 መንግስት በትግራይ ክልል እየወሰደ ስላለው ህግ የማስከበር እርምጃ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  መሰረታዊ መነሻው ምን እንደሆነ ትክክለኛውን  መረጃ ይፈልጋል።  ለዚህ ደግሞ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚሰጡት ሚዛናዊና ትክክለኛ መረጃ ወሳኝ ነው።  በሰሞኑ ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊነትን ያልጠበቁ ዘገባዎች ብሎም ከእውነት የራቁ መረጃዎች ሲያሰራጩ የሰነበቱትን ያህል እውነታውን ለማሳወቅ ታሪካዊ ዳራውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስገንዘብ ጥረት ያደረጉም ነበሩ። ከእነዚህም መካከል  ፎሬይን  ፖሊሲ መፅሔት ይገኝበታል።

 ፎሬይን ፖሊሲ መፅሔት በአሜሪካ የሚታተምና በዓለም አቀፋዊና  ወቅታዊ  ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ

ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ መገናኛ ብዙሃን መካከል አንዱ ነው።  መጽሔቱ በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ

አስመልክቶ ከሰሞኑ ሰፋ ያለ ትንታኔ አስነብቧል። መፅሔቱ “Tigray’s War Against Ethiopia Isn’t About

Autonomy. It’s About Economic Power.” በሚል ባስነበበው ትንታኔ የዚህ ቡድን ትክክለኛ ፍላጎት ምን እንደሆነና ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ወደግጭት የገባበትን መሰረታዊ ምክንያት እንደሚከተለው አቅርቧል።

 መንግስት በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ዘመቻ ከጀመረ ሶስት ሳምንታት አልፏል። አንዳንድ ተንታኞች ይህ ህግ

የማስከበር እርምጃ ሊሰፋና ኢትዮጵያን ወደመበታተን ሊያመራት ይችላል፤ ይህም በሁሉም የአፍሪካ ቀንድ አገራት ላይ ከፍተኛ  ፖለቲካዊና  ኢኮኖያዊ  ተጽእኖ  ያሳድራል  በማለት  ግምታቸውን  ሲናገሩ  ሰንብተዋል።  ነገር ግን በትግራይ ክልል እየተካሄደ ላለው ህግ የማስከበር ዘመቻን በተመለከተ  መሰረታዊ መነሻዎች ላይ ብዥታ  አለ በማለት ይገልጻል።

መጽሔቱ  እንዳስነበበው ከውጭ  ሆነው  ጉዳዩን  የሚከታተሉ አንዳንድ ታዛቢዎችና ተንታኞች በህወሃት እና በፌዴራል መንግስቱ መካከል ያለው ልዩነት  መንስኤው በቅርቡ በኮቪድ-19 ምክንያት በፓርላማ እንዲራዘም የተወሰነው ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ አለመግባባት አድርገው ይገነዘቡታል። ህወሃት ውሳኔውን ወደጎን በመተው በራሱ ክልል ያካሄደውና ሙሉ በሙሉ አሸንፌበታለሁ ያለው ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለው በመገለጹ የተፈጠረ ልዩነት አድረገው እንደሚያስቡትም አክሎ ይገልጻል።  ሌሎች ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድና በህወሃት ቡድን መካከል  ባለው የርዕዮተዓለም ልዩነት እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ አለመግባባቶች ልዩነት እንዴት ጦር ወደ መማዘዝ ሊሸጋገሩ እንደቻሉ አያብራራም።  ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የችግሩ መነሻዎች እነሱ ስላልሆኑ ነው - ይላል ትንታኔው።

ጉዳዩ በዋናነት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ፣ የተፈጥሮ ሀብቷን እና አገሪቱ በየአመቱ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች እና አበዳሪዎች

የምታገኘውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለመቆጣጠር የሚደረግ ፍልሚያ ነው ሲል አስገንዝቧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ወደ ስልጣን እስከመጡበት ጊዜ ድረስ የመንግስትን ስልጣን በበላይነት ሲመራ የነበረው ህወሃት ለሦስት አስርት  ዓመታት ያህል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በበላይነት ሲቆጣጠር እንደነበር ያስታውሳል። በመሆኑም ይህን ሀብት ለማስተዳደር የፌዴራል መንግስት ስልጣን መያዝ ወሳኝነት እንዳለው በመጥቀስ  ትንቅንቁ ይህን ስልጣን መልሶ ለማግኘት የሚደረግ ነው ሲል ይገልጻል። በሌላ አገላለጽ  ፍልሚያው  ከጠቅላላው 110 ሚሊዮን ከሚደርሰው የሀገሪቱ ህዝብ 6 በመቶ የሚሆነውን ህዝብ የሚኖርበትን የትግራይ ክልል ለማስተዳደር አይደለም። ይልቁንስ ትንቅንቁ ለረጅም አመታት ይዘውት የቆዩትንና በማንኛውም መንገድ መልሰው ለማግኘት እየታገሉለት ያለውን  በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የማዘዝ ስልጣንን መልሶ የማግኘት ጉዳይ ነው ሲል  ትንታኔውን  ያስቀምጣል። 

ህወሃት የደርግ ወታደራዊ  አስተዳደር  ከተወገደ  በኋላ ለ30 ዓመታት ያህል በአገሪቱ  ፖለቲካዊና  ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የበላይነት ይዞ መቆየቱን   የፎሬይን  ፖሊሲ ትንተና  አስታውሷል።

ጠቅላይ  ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ  አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የሀገሪቱ የደህንነት እና ወታደራዊ አዛዦች ሙሉ በሙሉ የህወሃት አባላት ወይም ደርግን ለመጣል በተደረገው  የትጥቅ  ትግል  የቡድኑ  የውጊያ  ክንፍ ውስጥ የነበሩ እንደነበሩም  ያስረዳል።  ከደርግ ውድቀት በኋላ ቡድኑ ነባሩን የመከላከያ ሰራዊት በመበተን የራሱን ጦር ወደሰራዊትነት መቀየሩንም ያስታውሳል። ይህ ደግሞ በጦሩ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ አመራሮችን በሙሉ በእነሱ ሰዎች እንዲያዙ ማድረጉን ያስረዳል።

ቡድኑ በፖለቲካና በወታደራዊው መስክ  ያገኙት  ብልጫ የሀገሪቱን ኢኮኖሚና የተፈጥሮ ሀብቶች - በዋናነትም መሬት -እና  የውጪ እርዳታና ብድር ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠሩ በዚህም የኢኮኖሚ የበላይነታቸውን እንዲያረጋግጡ አስችሏቸዋል።  በቅርብ አመታት እንኳን አገሪቱ በየዓመቱ 3.5 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የውጭ እርዳታ ታገኝ ነበር። ይህ የገንዘብ መጠን በቀድሞው ጠቅላይ  ሚኒስትር  መለስ  ዜናዊ  ጊዜ  የነበረውን  የአገሪቱን ጥቅል አገራዊ ምርት (GDP) ግማሽ እንደሚያህልም ያስረዳል።  

የህወሃት አመራሮች ከግል አበዳሪዎች እና ከተለያዩ  አገር  መንግስታት በተለይም ከቻይና ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር እንደወሰዱም በትንታኔው አስገንዝቧል።  የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ መንግስት ወደ ስልጣን በመጣበት ወቅት አገሪቱ ያለባት የውጭ ብድር መጠን  ከጠቅላላ  አገራዊ  ምርቱ 60 በመቶውን ይዞ እንደነበርም ጽሑፉ ያስረዳል።

በጣም አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ እዳውን የሚከፈልበትን ሁኔታ ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። በዚህም የተነሳ የመክፈያ ጊዜ በሚራዘምበት ሁኔታ ከአበዳሪዎች ጋር ለመነጋገር መገደዳቸውን አስታውሷል።

ፎሬይን ፖሊሲ በትንታኔው መሬት የህዝብ እንደመሆኑ የሚደነግገውን  ህገ-መንግስት በመጠቀም  በተለያዩ  የአገሪቱ

አካባቢዎች በተለይም በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ  እና  በጋምቤላ ክልሎች ሰፋፊ መሬቶችን ለውጪና  የአገር ውስጥ

ባለሀብቶች በመስጠት ባለስልጣናቱ  በቢሊዮኖች  የሚቆጠር  ዶላር  አጋብሰዋል  ይላል። ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እ.አ.አ በ2011 ባወጣው ሪፖርት በወቅቱ መንግስት 3.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሊዝ ሸጧል።

በሊዝ የተሸጠው መሬት ኔዘርላንድን የሚያክል ስፋት ያለው መሆኑን በመጥቀስ ህወሃት መሬትን እንዴት ለግል ጥቅሙ ሲያውል እንደነበር አሳይቷል።

ከዚህም በላይ ህወሃት እንደ ኤፈርት የመሳሰሉ ኩባንያዎችን በመጠቀም ሁሉንም የኢኮኖሚ መስኮች እንዴት

ሲቆጣጠር  እንደነበር  አመልክቷል።  ለዚህም በማሳያነት በስሩ በርካታ ኩባንያዎችን የያዘውና  በአገሪቱ ግዙፍ ከሚባሉት መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ኤፈርት እስከ  ቅርብ ጊዜ ድረስ  በወ/ሮ አዜብ መስፍን (የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር  መለስ  ዜናዊ  ሚስት) ሲተዳደር መቆየቱንና በርካታ የህወሃት አመራሮች አሁንም በስሩ ያሉ ድርጅቶች  የቦርድ አባል መሆናቸውን አንስቷል።  እነዚህ በልማት ስም የተቋቋሙ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ልማት ባንክ የሚፈልጉትን ያህል ገንዘብ ያለከልካይ በብርድ መልክ ሲያገኙ እንደነበርም አያይዞ ገልጿል።

የህወሃት አመራሮች የበላይነት በኢኮኖሚው መስክ ብቻ ተወስኖ እንዳልቀረ የሚተነትነው መጽሔቱ ማህበራዊ

መስኮችንም ለመቆጣጠር እንዲረዳው ዋና ዋና እምነቶች ላይ ጣልቃ በመግባት መሪዎችን እስከመምረጥ

መድረሳቸውንም ያስረዳል።  ለአብነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትሪያርክን ከትግራይ ክልል መሾሙን እንዲሁም የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች ምርጫ ላይ ጣልቃ መግባቱን አብራርቷል።  በተለይ ከእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሰፊ ተቃውሞ  የገጠመው  መንግስት በርካቶችን ለእስር ዳርጎ  እንደነበርም  አስታውሷል።

በህወሃት ሊቀመንበር መለስ  ዜናዊ አመራር  ዘመን  መሰረቱን  በዋነኛነት  በውጭ  ዕርዳታ  እና  በብድር  በሚገኘው ገንዘብ በማድረግ በሰፋፊ የመሰረተ ልማት፣ የትምህርት እና የጤና ዘርፎች ለሶስት አስርት ዓመታት ገደማ በሀገሪቱ ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት ቢመዘገብም በፍትሃዊ  ክፍፍሉ  ረገድ ችግር  የነበረበት እንደነበር  ፎሬይን  ፖሊሲ አልሸሸገም።

የህወሃት አስተዳደር ጨቋኝ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ለእስርና

እንግልት ሲዳርግና የተቃውሞ ሰልፎችን የጸጥታ ኃይሎችን በመጠቀም ሲያፍን እንደነበር ገልጾ  እንደ  አምነስቲ

ኢንተርናሽናል  የመሳሰሉ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት የመንግስት የጸጥታ

ሃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ  የሰብአዊ  መብት  ጥሰት  እንደሚፈጽሙ  ሲከሱ  እንደነበር ያስታውሳል። 

ምንም እንኳን አሜሪካ መንድሥትና የአውሮፓ ህብረት የመንግስትን ደካማ  የሰብአዊ  መብት አያያዝ  ቢያውቁም፣

በአገሪቱ በመሰረተልማት  ላይ  በስፋት ሲፈስ የነበረው ሀብት ያመጣው የኢኮኖሚ እድገት እና በሶማሊያ  የአልሸባብ

ታጣቂዎችን ለመዋጋት ኢትዮጵያ  ያላትን  ቁልፍ  ሚና  ታሳቢ  በማድረግ  በህወሃት  የሚመራው መንግስት ዴሞክራሲያዊ

ለውጥ  እንዲያመጣ  ከመጫን  ተቆጥበዋል።

 በምርጫ 97 የመንግስት ወታደሮች የምርጫ ውጤት ተጭበርብሯል በማለት ተቃውሞ ለማሰማት በወጡ ዜጎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውንና ግድያ መፈጸማቸውን እያወቁ እንኳን እንዳላዩ አልፈዋል በማለት ገልጿል። ከአምስት ዓመት በኋላ በተካሄደው ቀጣዩ ምርጫ ላይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጭበርብሯል ብለው  በከሰሱት ምርጫ  ህወሃት መራሹ መንግስት ሁሉንም  የፓርላማ  መቀመጫ  ማሸነፉን  ይፋ ሲያደርግም  ዝምታን መርጠዋል ብሏል።

 ይሁን እንጂ የህወሀት የፖለቲካ የበላይነት ለዘላለል እንደማይቀጥል ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግልጽ እየሆነ መጥቷል

ይላል።

 በ2010 በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ህወሃት መራሹ መንግስት ለረጅም ጊዜ ያደረሰውን ጭቆና በመቃወም

የተቀጣጠለው ተቃውሞ ህወሃት መራሹ  ፓርቲ  ሊቀመንበሩን  ለመቀየር እንዳስገደደው  ያትታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አመህድ ወደ ስልጣን መምጣት ለረጅም ጊዜ የአገሪቱን ፖለቲካ ሲዘውር የነበረው

ህወሃት ትግራይ ላይ ብቻ እንዲወሰንና የነበረውን የኢኮኖሚ የበላይነት የሚያሳጣ የኢኮኖሚ ማሻሻያም ማድረጋቸውን ያስታውሳል።

 በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙትን  ኢትዮ ቴሌኮምና  የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንን እንዲሁም ከሰባት

ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመቱትና  በኢነርጂ  ዘርፍ  የተሰማሩ  ሌሎች  ኩባንያዎችን ወደ ግል ለማዛወር የያዙት እቅድ

ከማሻሻያው ውስጥ እንደሚገኝ አስታውሷል።

በቅርቡ ደግሞ ነባሩን የብር ኖት በአዲስ  መተካቱን  ያስታወሰው  ትንታኔው  ዓላማውም  በቀድሞ የመንግስት

ባለስልጣናትና  በተቋሞቻቸው  አማካኝነት ለህገወጥ ንግድና  ህገወጥ ስራዎችን ለመደገፍ  ከባንክ ውጪ የሚዘዋወረውን ገንዘብ መቆጣጠር፣ ሙስናን ለመከላከል እና ኮንትሮባንድን መዋጋት መሆኑን አመልክቷል።

አያይዞም በቅርቡ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤህግ  ማንነት ላይ የተመሰረቱና የሽብር ጥቃቶችን በመደገፍ፣ ለህወሃት ድጋፍ በማድረግ፣ በሙስናና ታክስ ማጭበርበር 34 ድርጅቶች እንዲታገዱ መደረጉን አስታውሷል።  

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ መንግስት ያደረገው ማሻሻያ ህወሃት በደህንነት ረገድ የነበረውን የበላይነትም እንዲቀንስ አድርጓል ያለው የፎሬይን ፖሊሲ የደህንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋን ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው እና የጦሩ መሪም መቀየርን ተከትሎ በደህንነቱና በመከላከያ ላይ ሰፊ ማሻሻያ መደረጉን ያስታውሳል።

የእነዚህ ማሻሻያዎች መደረግ ህወሃት ለረጅም ጊዜ በኢኮኖሚውና ወታደራዊው መስክ ይዞት የቆየው የበላይነት ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ያነሳል። ከዛም ያጡትን መልሰው ለማግኘት  ትግል  ጀመሩ  ይላል   ትንታኔው።

ይህን ተከትሎ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች አለመረጋጋት መከሰት መጀመራቸውን የሚያስታውሰው ትንታኔው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን በመጡ ሶስት ወር ሳይሞላ በመስቀል አደባባይ  የድጋፍ ሰልፍ ለወጡ ሰዎች ንግግር በሚያሰሙበት ወቅት የግድያ ሙከራ እንደተደረገባቸው  ያስታውሳል።  የዚህ ጥቃት አቀነባባሪ የነበረው የቀድሞው የደህንነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ መሆናቸው ቢታወቅም አስቀድሞ  ወደ ትግራይ መሸሻቸውን ያስታወሰው ትንታኔው ግለሰቡ በግድያ ሙከራና በሰብአዊ መብት ጥሰት የፍርደ ቤት ማዘዣ ቢወጣባቸውም  የክልሉ መንግስት አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን ጽሑፉ አብራርቷል።

ህወሃት ስሥልጣኑን ማጣቱን ተከትሎ ከትግራይ በስተቀር በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተበራከቱ መጡ።

ምንም እንኳን በሀገሪቱ የብሔር ፉክክር ቢኖርም  ሁኔታው እንዴት  በሚሊዮን የሚቆጠሩ  ሰዎች  እንደተፈናቀሉ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች እና አማሮች እንደተጨፈጨፉና ቤቶቻቸው፣ ቤተክርስቲያኖቻቸው እና የንግድ ሥራዎቻቸው እንደወደሙ፤ የአማራ ብሔር ተማሪዎች እንደታገቱ፤ ወይም ከ150 በላይ ሰላማዊ ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት የሆነው የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እንደተፈጸመ  ያሳያል።

ከእነዚህ ጥቃቶች መካከል አብዛኛዎቹ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ወደ ስልጣን መምጣትና የማሻሻያዎቹን መተግበር ተከትሎ  ጥቅማቸው  የተነካባቸው  አካላት የተቀነባበሩና  በገንዘብ  የተደገፉ  ስለመሆናቸው ትንታኔው አብራርቷል።

አያይዞም እነዚህ አካላት አገሪቱን እነሱ ካልመሯት ለማስተዳደር የማትመች ለማድረግ  ቆረጠው  መነሳታቸውን ያብራራል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደስልጣን መምጣት የነበራቸውን ነገር ያጡት ብሎም እንዲህ አይነቶቹን የሽብር ተግባራት ለማቀድ፣ ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት የገነቡትን የገንዘብ አቅምና የደህንነት መዋቅር በመጠቀም ማስፈጸም የሚችሉት የህወሃት መሪዎች መሆናቸውን ትንታኔው ያስረግጣል።

አሁን ያለው ፍልሚያ ክልሉን ማን ያስተዳድር በሚለው ላይ አይደለም የሚለው ትንታኔው ለዚህም ምርጫውን

ለማራዘም የተወሰነው ውሳኔ በፌዴራል መንግሥቱና አስቀድሞም በህወሃት የምትተዳደረውን ትግራይን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ያሉ ህግ አውጪና አስፈጻሚ አካላትንም ቆይታ አብሮ ያራዘመ መሆኑን በማሳያነት ያሳያል።

በኢትዮጵያ የነበረው የፌዴራል ስርአት አሁንም በስራ ላይ እንዳለ ብሎም በቅርቡም 10ኛ ክልል መጨመሩን በማሳያነት በማንሳት ትግሉ  የአሃዳዊነትና ፌዴራሊስት ርዕዮተ ዓለም ጉዳይ  አለመሆኑንም  ጽሁፉ ይሞግታል።

ይልቁንም ትግሉ የሚያጠነጥነው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የፖለቲካና ኢከኖሚያዊ  ማሻሻያዎችና  እየተተገበሩበት

ያለው ፍጥነት ላይ ነው።  ህወሃት ለረጅም  ዓመታት  የነበረውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት የተገዳደሩትን እነዚህ ማሻሻያዎች እንደ ስጋት ቆጥሯቸዋል።  

በቅርቡ አንድ የህወሃት ባለስልጣን በመከላከያ ላይ የወሰዱትንና መንግስት እየወሰደ ላለው የህግ ማስከበር ዘመቻ

መነሻ የሆነውን ጥቃት “መብረቃዊ እርምጃ” ብለው መግለጻቸውን በማሳያነት በማንሳት ፍልሚያው ለረጅም ዓመታት በሀገሪቱ  የነበራቸውን  የኢኮኖሚና  የፖለቲካ የበላይነት መልሶ ለመቆጣጠር የሚያደርጉ ት ንቅንቅ  መሆኑን ያነሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም