መንግስት የሰላም ድርድር ሃሳብ ሊቀበል የሚችለው የህወሃት ጁንታ ለፍርድ ከቀረበ በኋላ ነው ... አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የሰላም ድርድር ሃሳብ ሊቀበል የሚችለው የህወሃት ጁንታ ለፍርድ ከቀረበ በኋላ ነው ... አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2013(ኢዜአ) “መንግስት የሰላም ድርድር ሃሳብ ሊቀበል የሚችለው የህወሃት ጁንታ ለፍርድ ከቀረበ በኋላ ነው” ሲሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
‘ኤ ቲቪ’ ከተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ማንኛውንም ልዑክ ተቀብሎ ያስተናግዳል።
“በተለይም ከጎረቤት አገሮች ብሎም ከአፍሪካ ልዑካን የሚመጣ ሙከራና ሃሳብ እንቀበላለን፤ ሁሉንም ወዳጆቻችንን እንሰማለን” ብለዋል።
ዋናው ነገር 200 ያህል የሚሆኑና የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው የህወሃት ጁንታ ጋር ድርድር የሚባል ነገር አለመኖሩን መረዳት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የላኩት ሶስት አባል ያለውን ልዑክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ነገ ተቀብለው እንደሚያስተናግዱም ጠቁመዋል።
ልዑኩን ተቀብለው ቢያስተናግዱም ህዝብ ከጨፈጨፈው፣ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸመው፣ የአገር ክህደት ከፈጸመውና በአገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ ሲያስተባብርና ሲመራ ከነበረው የህወሃት ቡድን ጋር የሚደራደሩበት ሁኔታ እንደማይኖር አምባሳደር ሬድዋን አስረግጠው ተናግረዋል።
ከቡድኑ ጋር መደራደር በኢትዮጵያ ለሰርጎ ገቦች መንገድ መክፈት እና ህገ ወጥነት እውቅና እንዲያገኝ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
በህግና ስርዓት የምትተዳደረው ኢትዮጵያ ወንጀለኛውን ቡድን ለህግ ካቀረበች በኋላ ማንኛውም ሰላም ሊያረጋግጥ የሚችል ድርድር ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ጠቁመዋል።
ከህወሃት ቡድን ጋር መንግስት ለድርድር ከተቀመጠ በኢትዮጵያ ህግና ስርዓት አስጠብቆ መቀጠል አደጋ ላይ እንደሚወድቅም ተናግረዋል።
በመሆኑም ህግን ለማስከበር የህወሃት ጁንታን ለህግ ለማቅረብ የህግ ማስከበር ዘመቻው እየተካሄደ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግስት ለትግራይ ክልል የበጀት ድጎማ እንዳይሰጥ ያደረገበትን ምክንያት በዝርዝር አብራርተዋል።
የህወሃት ቡድን የሚላክለትን በጀት ለልማት ከማዋል ይልቅ የጦርነት ዝግጅት ለማድረግ እያዋለ በመሆኑ በጀቱ በቀጥታ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ እንዲደርስ ለማድረግ መንግስት ውሳኔ አሳልፎ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ህወሃትና የትግራይ ህዝብ በፍጹም የተላያዩ መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን፤ “ህወሃት የፖለቲካ ቡድን ሲሆን ትግራዋያን ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል ናቸው” ብለዋል።
ፓርቲ የሚያልፍ እንደሆነ ጠቅሰው ህዝብ የነበረ፣ ያለና የሚኖር መሆኑን አስረድተዋል።
በትግራይ ክልል የፌዴራል መንግስት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ መጀመሩን ገልጸው፤ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ዳሰሳ መካሄዱንም ጠቅሰዋል።
ወደሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን ለመመለስ እየተሰራ እንደሆነ አንስተው፤ “እንኳንና የእኛን ዜጎች ይቅርና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሌሎች አገሮች ዜጎችን በስደተኝነት ተቀብለን እያስተናገድን ነው” ብለዋል።
በስደት ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ወደአገራቸው እንዲመለሱ የማግባባት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመው፤ ሊመለሱ የማይችሉት በማይካድራ ጭፍጨፋ እጃቸው ያለበት ወጣቶች ብቻ ሊሆኑ እንደሚችል ተናግረዋል።
ከመቀሌ በስተቀር ሁሉም የትግራይ አካባቢ ከህወሃት ቡድን ነጻ መውጣቱን ገልጸው፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራ እንደሚጀምርና ህዝቡ ወደመደበኛ ህይወቱ እንደሚመለስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።