በህወሃት ጁንታ ጥቃት ለተጎዱ የሰራዊቱ አባላትና በተለያዩ አካባቢዎች ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች ድጋፍ እየተሰባሰበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በህወሃት ጁንታ ጥቃት ለተጎዱ የሰራዊቱ አባላትና በተለያዩ አካባቢዎች ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች ድጋፍ እየተሰባሰበ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2013 (ኢዜአ)በህወሃት ቡደን ጥቃት የተጎዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በዘላቂነት ለማቋቋም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ድጋፍ ማሰባሰብ ጀምረዋል።
በህወሃት ጥቃት የተጎዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በዘላቂነት ለማቋቋም "የአገር ልጅ የማር እጅ" የሚል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ዛሬ ተጀምሯል።
የአገርን ዳር ድንበር በሚያስከብረው የመከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰው ጥቃት ጭካኔ የተሞላበትና ኢትዮጵያዊነትን የማይወክል እኩይ ድርጊት መሆኑን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
አንጋፋው የኪነ ጥበብ ባለሙያ አርቲስት አለማየው እሽቴ እንደገለጸው፤ አገሩንና ህዝቡን እየጠበቀ ባለው የመከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰው ጥቃት ተደርጎና ተሰምቶ የማያውቅ ክህደት ነው።
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በማንኛውም ጊዜ በአገርና በወገን ላይ የሚደርሰውን ችግር ተከትሎ ለሚቀርቡ የድጋፍ ጥሪዎች ግንባር ቀደም ሆነው ሲሰለፉ እንደነበርም አስታውሷዋል፡፡
አሁንም በሰራዊትና በመላው አገሪቷ ለጉዳት የተጋለጡ ዜጎችን ችግር ለመፍታት ከፊት እንሰለፋለን ብሏል።
በዚህም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ባለሃብቶችና ሁሉም ዜጋ አቅሙ የፈቀደውን ድጋፍ እንዲያደርግ በማስተባበር ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም መስራት ሙያዊና አገራዊ ግዴታችን ነው ብሏል።
በሰራዊቱ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረሰተብ ክፍሎችና በሌሎች አካባቢዎች የተጎዱ ዜጎችን በገንዘብና በቁስ ከማገዝ ባሻገር ፍቅር የተሞላ የልብ ወዳጅነት ልናሳያቸው ይገባል ሲሉ የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ መሐመድ ካሳ ተናግረዋል።
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ መርሃ ግብሩ በዋናነት ያዘጋጁት የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትንና በጥቃቱ ምክንያት የተጎዱትን የህብረተሰብ ክፍሎች አቅም በፈቀደ መልኩ ለመደገፍ መነሳታቸውንና አጋርነታቸውን ለማሳየት ነው ብለዋል።
በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ኢትዮጵያዊነትን የማይገልጽ እንደሆነና የኪነ ጥበብ ባለሙያው የህዝቡ የመተባበርና የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን ኮሜዲያን ተፈሪ መንግስቱ ተናግሯል፡፡
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ ዜጎች የሚችሉትን ያህል እንዲለግሱ ቃል በማስገባት ቃል የገቡ ሰዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሒሳብ ቁጥር 1000354217019 ገንዘቡን ገቢ ማድረግ እንደሚችሉም ተገልጿል።
በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የንግድ ባንኩን CBETETA ዓለም አቀፍ ስዊፍት ኮድ ተጠቅመው መላክ ይችላሉ ተብሏል ።
“ማር ምግብ ሆኖ ይበላል ምግቡ ሲያልቅ ሰሙ ብርሃን ይሆናል እኛ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ወደ ፊት የሚታየን የኢትዮጵያ ብርሃን ነው” ብለዋል አርቲስቶቹ በመልእክታቸው።