ድርብ ጥቃት - ኢዜአ አማርኛ
ድርብ ጥቃት
በአብዱራህማን ናስር (ኢዜአ)
በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን የምትገኘው ማይካድራ ከተማ የትግራይ፣ የወልቃይትና የአማራ እንዲሁም የሌሎች ብሄረሰብ ተወላጆችን ጨምሮ ከ45 እስከ 50 ሺህ የሚገመት ህዝብ ይኖርባታል። በዙሪያዋ ሰፋፊ የሰሊጥና የማሽላ እርሻ ቦታዎች ይገኛሉ። ወደ እነዚህ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች የጉልበት ስራ ለመስራት ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት ለተወሰኑ ጊዜያት ቆይተው ስራው ሲጠናቀቅ ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው መመለስ የተለመደ ነው።
የከተማው ነዋሪዎች አገር ሰላም ብለው የተለመደው የእለት ተእለት ተግባራቸውን በማከናወን ላይ እያሉ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም አንድ ያልታሰበ ድንገተኛ ክስተት ተፈጠረ። የማይካድራ ነዋሪዎች ቀን ጨለመባቸው። በአረመኔያዊ መልኩ በጅምላ ተጨፈጨፉ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከሕዳር 5 እስከ ሕዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በማይካድራ ከተማ እንዲሁም በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጐንደር ከተማ ተዘዋውሮ በድርጊቱ አፈፃፀም ዙሪያ ያደረገው ምርመራ ውጤት እንደሚያሳየው በማይካድራ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት ተራ ወንጀል ሳይሆን የታቀደ እና በጥንቃቄ ተቀነባብሮ የተፈጸመ እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ነው።
ጥቃቱ በተፈጸመበት እለት ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ጀምሮ በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆች በብዛት በሚኖሩበት ሰፈር የትግራይ የክልል ልዩ ሃይል አባላት በየቤቱ ፍተሻ በማካሄድ ነዋሪዎቹ መልዕክት እንዳያስተላልፉና የእርዳታ ጥሪ እንዳያሰሙ በማሰብ ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸውን በሙሉ ሰባብረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ጥቃቱ ከመጀመሩ ከጥቂት ሰዓታት አስቀድሞ በህወሓት የጥፋት ቡድን አስተባባሪነት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ በተለይ ሴቶች እና ሕፃናት ከተማዋን ለቅቀው እንዲወጡ መደረጋቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።
ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ የከተማው ፖሊሶች፣ ሚሊሻዎች እና ሳምሪ የሚባለው ኢ-መደበኛ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች ቡድን በአንድነት በመሆን ጥቃቱን መፈጸማቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አብራርቷል። ሳምሪ የሚባለው የወጣቶች ቡድን በአካባቢው ፖሊስና ሚሊሻ እየተደገፈ በየጎዳናው እና ከቤት ቤት በመዘዋወር አማራዎችና ወልቃይቴዎች ያሏቸውን ያልታጠቁ ሰዎች በከፍተኛ ግፍና ጭካኔ በዱላ በመደብደብ፣ በጩቤ በመውጋት፣ በገጀራና በፈራድ (ወይም ፋስ መጥረቢያ) በመምታት እና በገመድ በማነቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል፣ ንብረት ዘርፈዋል፣ አውድመዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት መሰረት እስከ 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥም እንደሚችል ተመላክቷል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥቃቱን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት በማይካድራ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት መፈጸሙን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች እንዳገኘ አስታውቋል። ድርጅቱ እንደገለጸው ማይካድራ ከተማ ውስጥ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ቁጥራቸው በመቶዎች ሊቆጠሩ የሚችሉ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተገድለዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በወቅቱ ያነጋገራቸው እማኞች ጥቃቱን የፈጸሙት ለህወሃት ታማኝ የሆኑ ኃይሎች መሆናቸውን ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በጥልቀት፣ በገለልተኝነትና በግልጽ መርምሮ ተጠያቂዎቹን ለፍርድ እንዲያቀርብም በሪፖርቱ ጠይቋል። በተጨማሪም የህወሓት አዛዦች በስራቸው ላሉ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ጥቃት ተቀባይነት የሌለውና የጦር ወንጀል መሆኑን ግልጽ ማድረግ አለባቸው ሲልም አስጠንቅቆ ነበር።
በተለያየ ደረጃ የሚካሄዱ የጅምላ ጭፍጨፋ ድንገት የሚደረግ ሳይሆን የተለያዩ ደረጃዎችን የሚያልፍና የቀደመው ለቀጣዩ እየመገበ የሚሄድ መሆኑን በመግለጽ ጄኖሳይድዎች የተባለ ድርጅት በ10 ደረጃዎች ከፋፍሎ አስቀምጦታል። በዚህ መስፈርት መሰረትም ተቋሙ በማይካድራ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ደረጃ ዘጠኝ “Extermination/ የዘር ማጥፋት” ላይ አስቀምጦታል።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከማይካድራው ጭፍጨፋ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ የህወሃት ጁንታ ቡድን ተመሳሳይ ዘግናኝ ጥቃት በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ አድርሷል። በሰሜን ዕዝ የነበሩት መኮንኖችና ወታደሮች መሳሪያቸውን ለማንሳት፣ ለመገመትም ሆነ ለመጠራጠር እንኳን ጊዜ ሳይኖራቸው የሠራዊቱ አባላት የሆኑት የትግራይ ተወላጆች ሠራዊቱን ከውጭ በትግራይ ልዩ ኃይል አስከብበው እነሱ ደግሞ ከውስጥ ሆነው ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ተኩስ ከፍተው በተኙበት ጨፍጭፈዋቸዋል። የመሳሪያ ዘረፋ ሙከራም አድርገዋል። መቀሌ የመሸገው የህወሃት ጁንታ በሚሰጠው ትእዛዝ የሚንቀሳቀሰው የትግራይ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የኖረውን የመከላከያ ሰራዊት እንደ ባዕድና ወራሪ ኃይል ቆጥሮ ከኋላው ወግቶታል፤ይህ ድርብ ጥቃት ነው።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የህወሓት ጁንታ የፈጸመው ጥቃት በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመ አሳፋሪ ድርጊት ነው። የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች የወከሉ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው። መከላከያ ሠራዊት አገርን ከውጭ ወረራና ጥቃት የሚታደግ፣ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚያስጠብቅና ሉዓላዊነት የሚያስከብር ነው። ይህን መሰል ተልእኮ በያዘ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸም አረመኔያዊነት ነው። በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘር የአገርንና የሕዝብን ክብር ከመናቅም አልፎ አገርን የሚያስደፍር ስለመሆኑ ምንም ማስተባበያ አያስፈልገውም። ለዚህም ነው መንግስት ህግን የማስከበርና የአገርን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በከሃዲው ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ ወደ መውሰድ የገባው።
የህወሃት የጥፋት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ዘግናኝ ጥፋት ሳያንሰው በማይካድራ ዘርን ለይቶ በንጹሐን ዜጎች ላይ ያደረሰው ርህራሄ የሌለውና ሰብአዊነት የጎደለው ዘግናኝ ጭፍጨፋ በዓለም አቀፍ ወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ሚሼል ባችሌት በማይካድራ ከተማ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ግድያ በማን እንደተፈጸመ መረጋገጥ ከቻለ እንደ ጦር ወንጀል ይቆጠራል ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ይህ የህወሃት አጥፊ ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ እንዲሁም በማይካድራ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው ጥቃት አልበቃ ብሎት አሁን ደግሞ ተመሳሳይ እልቂት በመቀሌ ለመፍጠር እየጣረ ይገኛል። ቡድኑ እያንዳንዱ የትግራይ ተወላጅ በስለትም ቢሆን እንዲዋጋ መልእክት ከማስተላለፍ ባለፈ ለጥፋት ያዘጋጃቸውን ሃይሎች የኢትዮጵያና ኤርትራ ሰራዊቶችን ልብስ ለብሰው ጥቃት እንዲፈጽሙ ለማድረግ እያተዘጋጀ ነው። ይሀንንም በማድረግ መንግስት ያልታጠቁ ሰዎችን እየገደለ ነው ብሎ ለመክሰስ እንዲሁም ኤርትራ ጦሯን አስገብታለች የሚለውን የውሸት ትርክቱን እውነት ለማስመሰል እየሰራ ይገኛል። ይህም ቡድኑ ምን ያህል ለጥፋት እየተዘጋጀ መሆኑን ማሳያ ነው።
ከሰሞኑ የቡድኑ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በክልሉ ሚዲያ ባስተላለፉት መልእክት ሁሉንም ዓይነት መሳሪያ በመጠቀም ጥቃት ለመፈጸም ከመቼውም ጊዜ በላይ መዘጋጀታቸውን ያለምንም ሀፍረት በግልጽ ተናግረዋል። አቶ ጌታቸው ረዳ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ አገሪቱ ልትበታተን እንደምትችል ሲያስፈራሩ የቆዩ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ሳንጃና ጩቤን ጨምሮ ማንኛውም ስለት ያለው መሳሪያ እንዲጠቀሙ መልእክት አስተላልፈዋል። ይህ መልእክት ሌላ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ነው።
በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ፤ የህወሃት ጁንታ ቡድን በማይካድራ የፈጸመውን ጭፍጨፋ በመቀሌ ለመድገም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ቡድኑ ድርጊቱን የሚፈጽመው ልዩ ቡድን በማዘጋጀትና በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ያዘጋጀውን የመከላከያና የኤርትራ ሠራዊት ዩኒፎርሞችን በማልበስ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ይህ ሁሉ ጥፋት ለምን?
ኢህአዴግ ሀገሪቱን ባስተዳደረባቸው 27 ዓመታት የህወሃት ቡድን በአገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ቁልፍ ሚና እንደነበረው ይታወቃል። በእነዚህ ዓመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮች እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ተቃውሞ እየበረታ በመምጣቱ ከሁለት ዓመት በፊት ለውጥ እንዲመጣ አስገድዷል። በሀገሪቱ የተገኘው ለውጥ በውስጥና በውጭ ባሉ መላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ እፎይታን የፈጠረ ነበር። ይሁን እንጂ የስልጣን ፍላጎት የነበራቸውና በስልጣን ለመቆየት የሚመኙ አካላት ማንኛውም መስዋእትነት ከፍለው ለውጡን ለመቀልበስ ማሴር የጀመሩት ጊዜ ሳይወስዱ ነበር።
ከመጀመርያውም ለውጥ ፈልጎ የማያውቀው የጁንታው ቡድን በፌዴራል መንግስቱ ሲከናወኑ የነበሩ የለውጥ አንቅስቃሴዎችን በተለያየ መልኩ ሲያጥላላና ሲያንቋሽሽ ከርሟል። ይህንን ፀረ-ለውጥ አቋሙንም ኢህአዴግ ፈርሶ አጋር ድርጅቶችን ያካተተው የብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት ከውህደቱን አሻፈረኝ ብሎ በመውጣት አረጋግጧል። ይህን ተከትሎም የፌዴራል መንግስቱን “አሃዳዊ፣ ፀረ-ፌዴራሊስት፣ ፀረ ህገመንግስት” በማለት መፈረጁን ተያያዘው። ከሌሎች መሰሎቹ ጋር ጥምረት በመፍጠር በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች መረጋጋት እንዳይኖር ማድረጉን ቀጠለ። በማህበራዊ ሚዲያ ‘አምባገነን መንግስት፣ የነፍጠኛ ሥርዓት አራማጅ’ ወዘተ ቃላትን በመጠቀም የሃሰት ፕሮፖጋንዳዎችን በማሰራጨት የፌዴራል መንግስቱን ሲያጥላላ ቆይቷል። ከፌዴራል መንግስቱ የሚወርዱ መመሪያዎችን ሁሉ ወደ ጎን በመተው ከሌሎች ክልሎች ወጣ ባለ መንገድ የራሱን አካሄድ መከተል ጀመረ። በመጨረሻም በኮቪድ ምክንያት የህገ መንግስት ትርጉም በመስጠት ፓርላማው ያራዘመውን ምርጫ ውድቅ በማድረግና ከህገመንግስቱ ፍጹም ባፈነገጠ ሁኔታ የራሱን የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ምርጫ እስከማካሄድ ደረሰ። ይህ ሁሉ ውጣውረድ በህዝባዊ ማእበል ያጣውን የስልጣን መዋቅር መልሶ ለመቆናጠጥ ካለው ጽኑ ፍላጎት የመነጨ እንጂ ለህዝቡ ተጨንቆ አይደለም።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በፎሬይን ፖሊሲ መጽሔት ባስነበቡት ጽሑፍ የህወሃት አመራሮች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ከፌዴራል መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባት በባለፈው እና በአሁኑ ጥፋታቸው ተጠያቂ ላለመሆንና ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎችን በመጠቀም ዳግም ወደስልጣል ለመምጣት እንደሚመኙ ገልጸዋል። አቶ ሃይለማርይም አያይዘውም ለ27 ዓመታት በህወሃት የበላይነት ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ ኢኮኖሚውና ፖለቲካውን በተገቢው መንገድ ባለመምራቱ በህዝባዊ አመጽ ለውጥ መምጣቱን አብራርተዋል። እናም የህወሃት የጥፋት ቡድን መከፈል ያለበትን ማንኛውም ዋጋ ለመክፈል እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየው ዳግም ወደ ስልጣን ለመመለስ ካለው ፍላጎት የመነጨ ስለመሆኑ ብዙዎቹ የፖለቲካ ተንታኞች የሚስማሙበት ነው።
የህወሃት የጥፋት ቡድን ዳግም ወደ ስልጣን ለመምጣት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያጋጠሙ ክስተቶች በሀገሪቱ ታሪክ ታይተው የማይታወቁና ለማህበረሰቡ እንግዳ ነገሮች ነበሩ። እነዚህ ክስተቶች ሊሰፉ ይችላሉ ተብሎ በብዙዎች ተገምቶ የነበረ ቢሆንም በህብረተሰቡ አስተዋይነት በቀላሉ ሊከስሙ ችለዋል። የችግሩ ጠንሳሽና አድራጊ ፈጣሪ ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን ግን በመከላከያ ሰራዊት ላይ በፈጸመው ጥቃት ግብዓተ መሬቱን ወደማፋጠን ተቃርቧል። ቡድኑ በመከላከያ ሰራዊት እና በማይካድራ በንጹሃን ዜጎች ላይ ለፈጸመውና ላስፈጸመው ግፍና ጭካኔ የተሞላበት የጭፍጨፋ ወንጀል በሕግ ፊት ቀርቦ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል። ቸር ያሰማን!