የሳሲጋ ወረዳ ነዋሪዎች 27 ሠንጋዎችን ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የሳሲጋ ወረዳ ነዋሪዎች 27 ሠንጋዎችን ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አደረጉ
ነቀምቴ፣ ህዳር 17/2013 (ኢዜአ) በምሥራቅ ወለጋ ዞን የሳሲጋ ወረዳ ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን የደጀንነት ድጋፍ ለመግለጽ 27 ሠንጋዎችን ማበርከታቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ አስታወቁ ፡፡
አስተዳዳሪው አቶ ደረጀ ድርበባ እንዳሉት የወረዳው ነዋሪዎች የህወሃት ጁንታ በሀገር መከላከያ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ከማውገዝ ጀምሮ ለሠራዊቱ ያላቸውን አጋርነቸውን በተግባር እየገለጹ ነው፡፡
ይህም ገንዘብ አዋጥተው የገዟቸውን 27 ሠንጋዎች ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ በግንባር ተሰልፈውም ህግ በማስከበሩ ተግባር ከሠራዊቱ ጎን ተሠልፈው ለማገዝ ዝግጁነታቸውን እያሳዩ መሆኑን አስረድተዋል።
የምሥራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደረጀ አበራ ከወረዳው ነዋሪዎች የተበረከቱት ሠንጋዎች ለምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የኢንዶክትሪኔሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ተወካይ ባስረከቡበት ወቅት ህዝቡ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል የገመቺስ ቀበሌ ነዋሪ አባ ገዳ ደረጀ ቀዲዳ በሰጡት አስተያየት ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል መሆኑን በመጥቀስ ጁንታው በሠራዊቱ ላይ የሰነዘረውን ጥቃት አውግዘዋል።
አሁን ካደረጉት ድጋፍ በተጨማሪም ለሠራዊቱ የደጀንነት እገዛቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል ።
በወረዳው የበረዳ ከተማ ነዋሪ አቶ በላይ ታምሩ በበኩላቸው አሁን ያደረጉት ድጋፍ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አለመሆኑን ገልጸው፣ ለወደፊቱም ከዚህ በበለጠ ሠራዊቱን እንደሚያግዙ ተናግረዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ሕግን ለማስከበር የጀመረውን ተግባር በስኬት እስኪያጠናቅቅ የሚፈለግባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የጋሎ ከተማ ነዋሪ አቶ አሸናፊ ጣአ ናቸው ፡፡
በድጋፍ አሰጣጡ ሥነ-ሥርዓት የዞኑና ወረዳ አመራሮች ፣የሠራዊቱ ተወካዮች፣ አባገዳዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።