የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ተመሰረተ
ህዳር 17/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ዛሬ መመስረቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።
ብሔራዊ ኮሚቴው የተቋቋመበት ዓላማ በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገራችን ወጥተው በባዕድ ሀገራት የሚገኙ ቅርሶችን በማጥናት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር በወዳጅነትና በመግባባት መንፈስ፤ ያም ካልሆነ ዓለም አቀፍ ህግን ማዕከል አድርጎ ቅርሶቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግን እንደሆነ ተገልጿል።
በምስረታ ጉባዔው ላይ ተገኝተው መድረኩን የከፈቱት የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ኂሩት ካሳው ‹‹ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ምድረ ቀደምትነቷ የብዝኃ ባህልና ቅርስ ባለቤት ናት” ብለዋል።
ቀደምት አባቶች በጥበብ የተራቀቁባቸውን ብዙ ቁጥር ያላቸውን ቅርሶች፣ ስዕላት፣ ንዋዬ ቅድሳት፣ መጻሕፍት፣ የወታደርና የሲቪል አልባሳት፣ የጦር መሳሪያዎችና ሌሎችም ቅርሶችን በስጦታ፣ በስርቆት እና በጦርነት ዝርፊያ ወደ ውጭ ሀገሮች መሄዳቸውን አስታውሰዋል።
ተጠሪነቱ ለሚኒስቴሩ የሆነው ብሔራዊ ኮሚቴ የሀገሪቱን የቅርስ ሀብቶች ከያሉበት አጥንቶ እንዲያስመልስ ታላቅ ሀገራዊ አደራ እንደተጣለበት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ የራሱ ጽህፈት ቤት የሚኖረው ሲሆን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአማካሪዎች ቡድን ይኖረዋል፡፡
ብሔራዊ ኮሚቴው አምስት ንዑሳን ኮሚቴዎች በስሩ የሚያዋቅር እንደሆነም ተጠቁሟል።
ብሔራዊ ኮሚቴው ከልዩ ልዩ ዘርፎች የተውጣጡ ምሁራን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ተመራማሪዎች እና ታዋቂ ሰዎችን ያካተተ 19 አባላት አሉት።