ቀጥታ፡

በኬንያ እና በማላዊ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለሰብአዊ ድጋፍ ገንዘብ ተሰባስቧል- አምባሳደር መለስ ዓለም

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2013 (ኢዜአ) በኬንያና በማላዊ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለሰብአዊ ድጋፍ የተሰባሰበውን ገንዘብ ወደ አገር ቤት ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጹ። 

"የህወሓት ቡድን" ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃትም ማውገዛቸውን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ለኢዜአ እንደገለጹት በሠራዊቱ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የአገር ህልውና ምሰሶ ላይ የተፈጸመ ክህደት ነው።

በዚህም በሁለቱ አገራት የሚገኙት ዜጎች ድርጊቱን በማውገዝ በህግ ማስከበር ሂደት መንግስት የሚወስደውን እርምጃ መደገፋቸውን አምባሳደር መለስ ገልጸዋል።

የሕግ ማስከበር እርምጃውን ተከትሎ ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ከኢትዮጵያዊያኑ የተሰባሰበውን ገንዘብ ወደ አገር ቤት ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የሕግ ማስከበሩ ሥራ ተጠናቆ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በጋራና በትብብር ለማጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ መግለጻቸውንም አምባሳደር መለስ ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኬንያ በነበራቸው ቆይታ ከኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።

የኬንያ መንግስት በትግራይ ክልል እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር እርምጃ በግልጽ እንደሚረዳና ኦፕሬሽኑ ባጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ ያለውን ተስፋ መግለጹንም አመልክተዋል።

ከሕግ ማስከበሩ በተጨማሪ በውይይቱ ሁለቱ አገራት ለ57 ዓመታት የዘለቀውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ትስስር ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለያዩ የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃውን አስመልክቶ ማብራሪያ በመስጠት ሚዛናዊና ትክክለኛ መረጃዎችን እያቀረቡ እንደሚገኙም አምባሳደር መለስ አስረድተዋል።

በተለይ ባለፉት ሳምንታት በኬንያ የሚገኙ ጋዜጦች በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው ተገቢውን ሽፋን መስጠታቸውን አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የምሁራን ስብስብ (ቲንክ ታንክ ግሩፕ) በሚያዘጋጇቸው መድረኮች ላይ በመገኘት ማብራሪያ እየተሰጠ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በቀጣይም በኬንያ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚያዘጋጇቸው መድረኮች ላይ በመገኘት የሕግ ማስከበር እርምጃውን በተመለከተ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም