በጋምቤላ ክልል በጁንታው ታቅዶ የነበረ የጥፋት ሴራ መክሸፉ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል በጁንታው ታቅዶ የነበረ የጥፋት ሴራ መክሸፉ ተገለጸ
ጋምቤላ፣ ህዳር 17/2013 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በህወሃት ጁንታ ታቅዶ የነበረ የጥፋት ሴራ በህዝቡና በጸጥታ ኃይሉ የተቀናጀ ጥረት ማክሸፍ መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።
ጁንታው በክልሉ ዘርግቶት የነበረውን የጥፋት መረብ ሙሉ ለሙሉ ለመበጣጠስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ለኢዜአ ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት፤ በጁንታው ታቅዶ የነበረው የጥፋት ሴራ መረጃ ቀድሞ በመድረሱ በጸጥታ ኃይል አስፈላጊው ጥናት ተካሄዶ ሴራውን ማክሸፍ ተችሏል።
“በዚህም ችግር ሊፈጥሩ የነበሩ አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል“ ብለዋል።
የህወሃት ጁንታ ሴል በክልሉ በብዛት እንደነበረ ያስታወሱት አቶ ኡሞድ፤ “ክልሉ የቡድኑ የጥቃት ኢላማ ይሆናል የሚል ስጋት በመኖሩ ሰፊ የመከላከል ስራ ተሰርቷል” ብለዋል።
አካባቢው የብጥብጥ ቀጠና እንዲሆን አቅዶ የነበረው የጥፋት ሴራ በህዝብና በጸጥታው ሃይሉ የተቀናጀ ጥረት ማክሸፍ መቻሉን አስታውቀዋል።
የቡድኑን ሴሎች በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ የቀሩ መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ቀሪዎቹን ለመያዝም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል።
ክልሉን ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኙ ስምንት የመውጫና መግቢያ በሮች መኖራቸውን አስታውሰው፤ የጥፋት ቡድኑ አባላት ወደ ደቡብ ሱዳን ለመኮብለል እየሞከሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ድንበር አቋርጠው ለመውጣት የሞከሩ የቡድኑ አባላት መያዛቸውን ጠቁመው፤ “የጥፋት ቡድኑን መንገድ በመምራት ለማሸሽ የሞከሩ ሶስት ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት በአካባቢው አስፈላጊው የጸጥታ ኃይል ተመድቦ የተጠናከረ ክትትልና ጥበቃ እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የጁንታውን ሴራ እስከ መጨረሻው ለማምከን በተጀመረው ህግን የማስከበር ስራ የክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በክልሉ ከህወሓት ቡድንና ኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 65 ግለሰቦች የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ሰሞኑን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ኢዜአ በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል።