ቀጥታ፡

የክልሉ ወጣት የአካባቢውን ሠላም መጠበቁን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ

ጋምቤላ፣ ህዳር 17/2013(ኢዜአ) የክልሉ ወጣት የአካባቢውን ሠላም ነቅቶ በመጠበቅ ያሳየውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ -ጉባኤ አቶ ጁሉ ኛንጋል አሳሰቡ ።

’እኩልነትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና’’ መሪ ሀሳብ 15ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ባተኮሩ ውይይቶችና ደም ልገሳ በክልሉ መከበር ጀምሯል።

አፈ- ጉባኤው በጋምቤላ ከተማ የወጣቶች የውይይት መድረክ ላይ እንዳሉት ህወሓት ባለፉት 27 ዓመታት በክልሉ ሲፈጽማቸው በነበሩት የመሬት ዘረፋና ብልሹ አሰራሮች በክልሉ የወጣቶች ተጠቃሚነት ላይ ተጽዕኖ ፈጥሮ አልፏል።

ለዚህም ዋነኛ ማሳያው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥሩ የተሰጣቸውን መሬት ለባንክ በማሲያዝ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገንዘቦችን ዘርፈው መጥፋታቸው ነው ብለዋል።

የህወሓት የጥፋት ቡድን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወጣቱን ለእኩይ ተግባሩ በመደለል የሰው ህይወትና ንብረት እንዲጠፋ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተው ሆኖም የክልሉ ወጣቶች በጁንታው ሳይታለሉ ከመንግስት ጎን በመቆማቸው የአካባቢው ሠላም መጠበቅ እንደተቻለ ገልጸዋል።

የክልሉ ወጣቶች በጁንታው ሳይደለል የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ በመጠበቅ ረገድ እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች መካከል ኡኮች ኡቹዶ በሰጠው አስተያየት ህወሓት ባለፉት ዓመታት የፈጸመው ግፍ፣ በደልና ዘረፋ ሳያንሰው በቅርቡ ሌላ ትርምስ ለመፍጠር አቅዶ የነበረ ቢሆንም መክሸፉን ተናግሯል።

በቀጣይም የዚህን የጥፋት ቡድን ሴራ ከመንግስት ጎን በመሆን ለማክሸፍ እንደሚሰሩ ገልጿል።

የጥፋት ቡድኑ ሲያራምደው የነበረው የከፋፋይ ፖለቲካ አካሄድ በማፍረስ አንድነትና ሀገሩን የሚወድ ዜጋ ለመፍጠር መንግስት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ያለው ደግሞ ወጣት ዳዊት ኃይሉ ነው።

ወጣት ሬት ባቶም በበኩሉ የጁንታው ሴራ ቀደም ሲል የሚታወቅ ቢሆንም በሚያደርሰው ተጽዕኖ ህዝቡ ዝምታን መርጦ መቆየቱን ተናግሯል።

በተለይም የክልሉን መሬት ተቀራምቶ ለወጣቱ የስራ እድል የሚፈጥር መስሎ መሬቱን በማሲያዝ ገንዘብ ዘርፎ መሄዱን ጠቁሞ ቡድኑን ሥርዓት ለማሲያዝ ከሀገር መከላከያ ጎን ለመሰለፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

በውይይት መድረኩ የተለያዩ የመወያያ መነሻ ጹሁፎች ቀርበው ተሳታፊ ወጣቶቹ መክረውባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም