የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች ለሠራዊቱ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ሠንጋዎችና ግመል አበረከቱ - ኢዜአ አማርኛ
የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች ለሠራዊቱ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ሠንጋዎችና ግመል አበረከቱ
ሐረር፣ ህዳር 17 /2013(ኢዜአ) የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ እንዲውሉ ከሶስት ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ 94 ሠንጋዎች እና አንድ ግመል አበረከቱ::
ከነዋሪዎቹ የተበረከቱት ሠንጋዎችና ግመል የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሐላፊ አቶ አብዱልጀባር መሀመድ ለምስራቅ እዝ መከላከያ ሠራዊት ተወካይ ኮሎኔል ሐሰን ሰዒድ አስረክበዋል።
አቶ አብዱልጀባር በርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንደተናገሩት ጁንታው በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት እለት ጀምሮ የክልሉ ህዝብ የቡድኑን የጥፋት ድርጊት እያወገዘ ለሠራዊቱ ያለውን አጋርነት የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እየገለጸ ነው።
በክልሉም ባለፉት 15 ቀናት ውስጥ ከፍተኛ አመራሩ፣ የመንግስት ሰራተኛውና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ቃል ከገቡት 26 ሚሊየን ብር ውስጥ 16 ሚሊዮን ወደ ባንክ ሂሳብ መግባቱን አስረድተዋል።
ህብረተሰቡ በገንዘብና ዓይነት እንዲሁም ደም በመለገስ የሚያደርገው ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ከፍተኛ መነሳሳት እንዳለው አቶ አብዱልጀባር ተናግረዋል።
ኮሎኔል ሐሰን ሰዒድ በበኩላቸው የሠራዊቱ ጀግንነት የሚመነጨው ከጀግናው ህዝባችን ነው፤ ከዚህ ጀግና ህዝብ በመፈጠራችን ደስተኞች ነን፤ ለህዝባችን የማንከፍለው መስዋዕትነት የለም ብለዋል።
በሰሜን በኩል ሠራዊቱ በጥሩ ጀግንነት የህግ የማስከበሩን ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው በቅርብ ቀንም እብሪተኛው ጁንታ ተይዞ ለፍርድ እንደሚቀርብ ጥርጥር እንደሌለው ገልጸዋል።
በተለይ ህብረተሰቡ በውስጡ ተደብቀው ሽብር ለመፍጠር የሚያስቡ የኦነግ ሸኔና የጁንታው ህወሃት ተላላኪዎችን በማጋለጥ ህግን ለማስከበር ከመንግስትና ሠራዊቱ ጋር በቅንጅት እንዲሰራም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በድጋፍ ርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ከተገኙት የከልሉ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አበበች ዮሴፍ በሰጡት አስተያየት መከላከያ ሠራዊቱ እያስመዘገበ በሚገኘው ህግ የማስከበር ድል እጅግ ተደስቼያለው ብለዋል።
አሁንም ሆነ በቀጣይ ለሠራዊቱ በሚከናወነው የድጋፍ ስራ ላይ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለሠራዊቱ ደም የመለገስ፣ ሠንጋዎችንና ሌሎችን ድጋፎች በማሰባሰብ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ አካሉ ጥበቡ ናቸው።
የድጋፉ ስራ ህግ የማስከበሩ ስራ በስኬት እስኪጠናቀቅ ድረስ እንደሚቀጥሉበት ጠቁመው በተለይ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መርዳት እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።