የህወሃት ቡድን ጀንበሯ ስትጠልቅበት የትግራይን ህዝብ መደበቂያ ማድረጉ ፍፁም ተቀባይነት የለውም- የክልሉ ተወላጆች

92

አዲስ አበባ ህዳር 16/2013 (ኢዜአ) የህወሃት ቡድን ጀንበሯ ስትጠልቅበት የትግራይን ህዝብ መደበቂያ ማድረጉ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በአዲስ አበባ የሚኖሩ የክለሉ ተወላጆች ተናገሩ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የትግራይ ክልል ተወላጆች የህወሃት ጁንታ የሴራ ፖለቲካው ማብቂያ ላይ የትግራይን ህዝብ "ወገኔ" በማለት መደበቂያ ማድረጉ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

ቡድኑ ስልጣን ላይ በቆየባቸው አመታት ለትግራይ ህዝብ ሳይሆን ለራሱና ቤተሰቡ ጥቅም ብቻ ሲሰራ ቆመየቱንም ገልጸዋል።

የክልሉ ህዝብ የሚጠጣው ንጹህ ውሃ እንኳን ሳይቀርብለት፤ በርካቶች በችግር ባለበት የህወሃት ጁንታ ቡድንና ቤተሰቦቹ ግን ኑሯቸውና የኢኮኖሚ አቅማቸው ምን ላይ እንዳለ ለብዙዎች የሚታይ እውነታ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የትግራይ ህዝብ የተሻለ ፖለቲካ አማራጭ እንዳይኖረው "ህወሃት ወይም ሞት" እየተባለ ታፍኖ እንደኖረም አንስተዋል።

የህወሃት ቡድን አሁን ላይ "ጀንበሯ እየጠለቀችበት" መሆኑን ሲረዳ የትግራይን ህዝብ መደበቂያ ለማድረግ መሞከሩ በፖለቲካም፣ በሞራልም ተቀባይነት የለውም ይላሉ ወይዘሮ ባንች ፀሃየ ።

ከክልሉ ተወላጆች መካከል ወይዘሮ ሃና ምህረቱ እንዳሉት ደግሞ የህወሓት ቡድን ስልጣን የሚያጋራው አንኳን አብረውት ለታገሉት ሳይሆን ለዘመዶቹና ደጋፊዎቹ ብቻ ነበር።

ለኢትዮጵያ ነፃነት ሲሉ አብረውት የታገሉ በርካታ ጀግኖችን በማራቅና በማስወገድ በተንኮልና ሴራ አስካሁን መቆየቱንም አስታውሰዋል።

ይህንን ከሃዲ ቡድን በተለይ ወጣቱ፣ የትግራይ እናቶችና አባቶች የማይቀበሉትና አሳልፈው የሚሰጡት ስለመሆኑም ገልጸዋል።

የህወሃት ጁንታ በራሱ ልሳኖች በተለይ በድምጸ ወያኔ እና የትግራይ ቴሌቪዥን የሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች የመነጠል ሙከራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ለእውነት የሚቆም ህዝብ ስለመሆኑ ወይዘሮ ባንች ነግረውናል።  

የቡድኑ ቁንጮ የሚባሉት በሚዲያ ቀርበው የሚያስተላልፉት የአመጽ ጥሪም ፈጽሞ ህዝቡ የማይቀበለው ስለመሆኑም አስተያየት ሰጭዎቹ ገልጸዋል።

አስተያየት ከሰጡን መካከል ወይዘሮ መቅደስ ተስፋ ኪሮስ እንዳሉትም የትግራይ ህዝብ እስካሁን በህወሃት ቡድን ታፍኖ እንጂ በደሉ የበዛ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የህወሃት ቡድን በትግራይ ህዝብ ስም እየማለ የሚሰርቅ፣ ለራሱ ብቻ የሚጠቀም፣ በሚቃወሙት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የማይራራ መሆኑንም አስተያየት ሰጭዎቹ ገልጸዋል።

አሁን ላይ የትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ ለመቅረብ የሚያደርገው ሙከራም እንደማይሳካለት አረጋግጠዋል።

መንግስት የህወሃትን ቡድን በጀመረው የህግ ማስከበር ሂደት በማስወገድ የትግራይ ክልል ህዝብ ያሉበትን መሰረታዊ ችግሮች እንዲፈታ ጠይቀዋል አስተያየት ሰጭዎቹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም