ቀጥታ፡

የፀረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ ከዛሬ ጀምሮ ለ16 ቀናት ይካሄዳል -- የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት

አዲስ አበባ ህዳር 16/2013 (ኢዜአ) በሴቶች ላይ የሚፈጸምን ጾታዊ ጥቃት የሚቃወም ዓለም አቀፍ ዘመቻ ከዛሬ ጀምሮ ለ16 ቀናት እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት አስታወቀ። 

ቅንጅቱ ዛሬን ጨምሮ ለ16 ቀናት የሚካሄደውን ጸረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ  ስጥቷል።

ዓለም አቀፍ ዘመቻው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን፣ "በኢትዮጵያ እነዚህን ቀናት በኅብረት በማሰብ በሴቶች ላይ ችግር እያደረሰ ያለውን ጾታዊ ጥቃት ለመግታት አገራዊ አጀንዳ ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሯ ጾታዊ ጥቃትን ለማስቀረት ተቀናጅቶ መስራት አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ገልፀዋል።

ለቀጣዮቹ 16 ቀናት የሚካሄደው የጸረ ጾታዊ ጥቃት እንቅስቃሴ የቅንጅት ሥራው አካል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህም የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም የሚሰሩ አካላትን በማሰባሰብ ልምድ ከመለዋወጥ ባለፈ በተገኙ ውጤቶችና ባጋጠሙ ችግሮች ላይ የጋራ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

"ዕለቱን አስመልከቶ በሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች የሚገኙ ሀሳቦችን በማደራጀት መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ለጉዳዩ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡት ይደረጋል" ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ ሴቶች እየደረሰባቸው ባለው ጾታዊ ጥቃት ምክንያት ማኅበራዊና ኢኮናሚያዊ ጫና  ውስጥ ከመግባታቸው ባሻገር በአገር ላይ የሚያስከትለው ጫናም ቀላል አይደለም።

በመሆኑም መንግስትና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን  ባለሙያዎች በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት አስመልክተው ተከታታይነት ያላቸው ሥራዎች መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

ለችግሩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለማስቆም ሁሉም የበኩልን መወጣት እንዳለበትም ወይዘሮ ሳባ አሳስበዋል።

የ16ቱ ቀናት ጸረ ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ በሴቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የዘንድሮው ፀረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ  "ሠላም ለሴቶች ከጓዳ እስከ አገር" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚከበረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም