መንግስት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ አስመልክቶ ወቅታዊና በቂ መረጃ ተደራሽ መሆን አለበት - የሕዝብ አስተያየት ጥናት - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ አስመልክቶ ወቅታዊና በቂ መረጃ ተደራሽ መሆን አለበት - የሕዝብ አስተያየት ጥናት
አዲስ አበባ ህዳር 16/2013 (ኢዜአ) መንግስት በህወሓት ፅንፈኛ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ አስመልክቶ ወቅታዊና በቂ መረጃ ተደራሽ ማድረግ እንዳለበት ኢዜአ ባካሄደው የሕዝብ አስተያየት ጥናት የተሳተፉ አስተያየት ሰጪዎች ገለፁ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መንግስት በህውሓት ጁንታ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር እርምጃ አስመልክቶ በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ የሕዝብ አስተያየት ጥናት አካሂዷል።
በጥናቱ ከአገሪቷ የተለያዩ ክልሎችና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ካጠናቀቁ እስከ ሁለተኛ ዲግሪና ከዛ በላይ ያላቸው ሰዎች ተሳትፈዋል።
በኢዜአ የስልጠና፣ ምክርና ምርምር ማዕከል ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ዳንጉል ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ፈጣን የኀብረተሰብ አስተያየት ጥናቶችን በመስራት ጥናቶቹ ያመላከቷቸውን ጉዳዮች ለሚመለከታቸው አካላት ማድረስ ከማዕከሉ ተግባራት ዋነኛው ነው ይላሉ።
ተቋሙ አዲስ መዋቅራዊ አደረጃጀት በመስራት ወደ ተግባር መግባቱን ተከትሎ የተቋቋመው ማዕከሉ ከመደበኛ ጥናቶች ባሻገር እስካሁን በኮቪድ-19፣ በሕዳሴ ግድቡ፣ በነባሩ የብር ኖት ቅያሪና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የሕዳሴውን ግድብ የተመለከተ አወዛጋቢ ንግግርን አስመልክቶ የኀብረተሰቡን እይታ የሚዳስሱ ጥናቶችን አካሂዷል።
ህገወጡ የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የፈፀመውን አረመኔያዊ ድርጊት ተከትሎ መንግስት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ አስመልክቶም ፈጣን የኀብረተሰብ አስተያየት ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ለማድረስ ያነሳሳውን ነገር በተመለከተ የተጠየቁት የጥናቱ ተሳታፊዎች በርካታ መላምቶችን ያቀረቡ ሲሆን ቡድኑ ጥቃቱን ለማድረስ ያነሳሳው ዋናው ነገር የተጀመረውን ለውጥ በማደናቀፍ አገርና መንግስት እንዲበተን ማድረግ ነው ይላል።
አስተያየት ሰጪዎቹ የጥቃቱ ዋና ግብ ቡድኑ የቀረበትን ጥቅምና ስልጣን መልሶ ለመቆጣጠር የሚያደርገው የጻረሞት ትግል ነው ማለታቸውንም አቶ ገዛኽኝ ጠቅሰዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደልና የንብረት ውድመት ያስከተሉ ግጭቶችም ህወሓት ከጀርባ እንዳለበት እንደሚያምኑ አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች ገልፀዋል።
አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ የወሰደው እርምጃ የውጭ ኃይል እጅ አለበት ብለው እንደሚያምኑ መግለፃቸውንም አብራርተዋል።
መንግስት በጥፋት ቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ በአገሪቷም ሆነ በቀጣናው ሠላም፣ መረጋጋት፣ የሕግ የበላይነት፣ የዴሞክራሲ ግንባታና ለሕዝቦች ትስስር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለውም ያስባሉ።
እየተወሰደ ያለው ሕግ የማስከበር እርምጃ ሲጠናቀቅ የቡድኑ ህልውና ከስሞ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ያስችላል ብለውም ያምናሉ አስተያየት ሰጪዎቹ።
የማዕከሉ የጥናትና ምርምር ቡድን መሪ አቶ ዳግም መርሻም አስተያየት ሰጪዎቹ መንግስት በህወሓት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አስመልክቶ ለአገር ውስጥና ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ወቅታዊና በቂ መረጃ እየሰጠ ነው ብለው አያምኑም ይላሉ።
ስለሆነም መንግስት በበለጠና በተጠናከረ ሁኔታ በየደረጃው መረጃ ተደራሽ ማድረግ እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎቹ ማመልከታቸውን ተናግረዋል።
ህወሓት እየተወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር እርምጃ እየደረሰበት ያለውን የሽንፈት ካባ ለመሸፋፈን ከሚጠቀምባቸው ስልቶች አንዱ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ብዥታና ጥርጣሬ መፍጠር እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎቹ መናገራቸውንም ገልፀዋል።
የህወሓትን ሀሰተኛና አደናጋሪ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለመመከት በትግራይ ሕዝብ ተወዳጅነትና ተቀባይነት ያላቸውን የማኅበረሰብ አባላት በመጠቀም ለሕዝቡ ወቅታዊና ተዓማኒ መረጃ በመስጠትና ሌሎች ስልቶችን በመጠቀም የሚሰራጨውን ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ማክሸፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ መንግስት ተደጋጋሚ የሠላም ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም የጥፋት ቡድኑ ከሴራ ፖለቲካ የማይላቀቅ በመሆኑ መንግስት ወደ ድርድር መመለስ የለበትም ብለውም ያምናሉ።
ሕገወጡ ቡድን ለሠላም ያለው አረዳድ የተዛባ መሆኑን ለሠላም ጥረት ያደረጉ አካላት የሚናገሩት ሀቅ በመሆኑ የሕግ ማስከበር እርምጃውን መቀጠልና ቡድኑን ለሕግ ማቅረብ ከመንግስት ይጠበቃል ብለዋል።
እየተወሰደ ካለው ሕግ የማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ አካላት የሚጠበቁ ሚናዎችን በተመለከተም አስተያየት ሰጪዎቹ የተለያዩ ሃሳቦችን አንስተዋል።
ከሃሳቦቹ መካከል የተጀመረውን ሕግ የማስከበር ስራ በፍጥነት መቋጨት፣ የራስን ሠላም ነቅቶ መጠበቅ፣ ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት፣ መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ማቅረብ የሚሉት ይገኙበታል።