የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከሱዳን አቻው ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከሱዳን አቻው ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ ህዳር 16/2013 (ኢዜአ) በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ውድድር (ሴካፋ) የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ዛሬ ከሱዳን አቻው ጋር ያካሂዳል።
የሴካፋ ውድድር በታንዛኒያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ ውድድር የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እየተካፈለ ሲሆን በምድብ ሦስት ከሱዳንና ኬንያ ጋር መደልደሉም ይታወቃል።
በዚህ ውድድር የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የምድቡን የመጀመሪያ ጨዋታ በኬንያ አቻው 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።
ቡድኑ የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ከሱዳን አቻው ጋር ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በታንዛኒያ የሚያደርግ ይሆናል።
ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍና ከነገ በስቲያ በሚካሄደው የሱዳን እና ኬንያ ጨዋታ ውጤትም ይወሰናል።