ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች አንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት አገኙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች አንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት አገኙ
አዲስ አበባ ሀምሌ 11/2010 22 ኢትዮጵያዊያን የአትሌቲክስ አሰልጣኞች ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት አገኙ። ከሰኔ 29 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና ትናንት ተጠናቋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በጋራ ያዘጋጁት ይህ ስልጠና ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 24 አሰልጣኞች ተሳትፈውበታል። ስልጠናውን የሰጡት በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአሰልጣኝ መምህርነት ደረጃ ያላቸው ሁለት አሰልጣኞች ሲሆኑ ከኢትዮጵያ አቶ አድማሱ ሳጂ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና ከኬንያ ሚስተር ሳሙኤል ላታባ ናቸው። ስልጠናው ትናንት በተጠናቀቀበት ወቅት ሰልጣኞቹ የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ፈተና ወስደዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አድማሱ ሳጂ ለኢዜአ እንደገለጹት ከ24 አሰልጣኞች 22ቱ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚያስችል ነጥብ አግኝተዋል። ቀሪዎቹ ሁለት አሰልጣኞች በተግባር ፈተናው ጥሩ ውጤት ቢያመጡም በንድፈ ሀሳብ ፈተና ዝቅተኛ ውጤት ማምጣታቸውን ተከትሎ የአሰልጣኝነቱን የምስክር ወረቀት አለማግኘታቸውን ጠቅሰዋል። ዓለም አቀፍ የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት የምስክር ወረቀት ያገኙት አሰልጣኞች ከ16 ዓመት በታች እድሜ ያላቸውን ጀማሪ አትሌቶች የማሰልጠን እውቅና እንዳገኙም ተናግረዋል። ስምንቱ አሰልጣኞች ከመቶ ድምር ውጤት ከ80 በላይ ውጤት በማምጣት በቀጣይ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና የመውሰድ እድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ቀሪዎቹ 14 አሰልጣኞች ከ70 በላይ ውጤት በማምጣት በቀጣይ በአህጉር አቀፍ ደረጃ በሚሰጡ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአሰልጣኝ መምህርነት ስልጠና ላይ እንደሚሳተፉም ነው አቶ አድማሱ ያስረዱት። የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና በኢትዮጵያ ሲሰጥ ከ2007 ዓ.ም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።