ቀጥታ፡

የመቀሌ ነዋሪዎች የህወሓት ጁንታ በቁጥጥር ስር እስኪውል ጥፋት እንዳያደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል- የትግራይ ተወላጆች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15/2013 (ኢዜአ) የህወሓት ጁንታ በቁጥጥር ስር እስኪውል ያገኘውን አጋጣሚ ተጠቅሞ የከፋ ጥፋት ሊያደርስ ስለሚችል የመቀሌ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል አሉ የትግራይ ተወላጆች።

ትግራይ ከብሄርተኝነት የጸዳ ጠንካራና አሳታፊ የሆነ አስተዳደር ያስፈልጋታል ብለዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ የትግራይ ተወላጆች መካከል አቶ ዮሐንስ ጎይቶም እንደሚሉት በትግራይ ስም ሲነግድ የኖረው የህወሓት ቡድን ከኢትዮጵያ ህዝብ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ የሰላም ጠንቅ ነው።

ቡድኑ ከራሱ ጥቅምና ፍላጎት ውጪ በሀሰት እታገልለታለሁ ለሚለው የትግራይ ህዝብ እንኳን ከሃፍረት ውጪ ያተረፈለት አለመኖሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው ብለዋል።

ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያቀደው እቅድ ሙሉ ለሙሉ እየከሸፈ በመሄዱ በዓለም ላይ ተደርጎ የማያውቅና የህዝብ መከታ በሆነ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም የሰላም ጠንቅነቱን በግልጽ አሳይቷል ነው ያሉት።

እንደ አቶ ዮሐንስ ገለጻ መንግስት ይህን ጸረ-ህዝብ ቡድን በአፋጣኝ በቁጥጥር ስር እስኪያውል ባገኘው አጋጣሚ የከፋ ጉዳት ማድረሱን አያቆምም ብለዋል።

 ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን አገሪቷን በመራባቸው ጊዜያት ያስገነባቸው መሰረተ ልማቶች ለራሱ ጥቅም ብቻ እንዲውሉ ታሳቢ በማድረግ ነው።

ለዚህ ደግሞ ቡድኑ ወደ ህግ የሚቀርብበት የመጨረሻ ሰዓት ላይ ሲደርስ ለትግራይ ብሎም ለኢትዮጵያ ህዝብ መጠቀሚያ ወሳኝ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥፋት ማድረስ መጀመሩን ለአብነት አንስተዋል።

ይህ ድርጊት ቡድኑ ከራሱ ጥቅም ውጪ ለማንም የማያስብ ስግብግብ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

አብዛኞቹ የትግራይ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መሆናቸውን አስታውሰው መቀሌ የተሸሸገው ቡድን በቁጥጥር ስር እንዲውል የመቀሌ ነዋሪዎች ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የቀድሞ የበረራ ደህንነት ባለሙያ ሻምበል ግርማይ ወልዱ በኩላቸው የህወሓት ቡድን ከውጭ ወራሪ ጠላቶች ጋር በመሆን የትግራይ ህዝብ ላይ ጉዳት ሲያደርስ ነበር ይላሉ።

''እነዚህ ሰዎች ከመጀመሪያውም አይደለም ለኢትዮጵያ ለትግራይም ህዝብ የሚበጁ አልነበሩም ያሉት ሻምበል ግርማይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከትግራይ ምድር ሊወገዱ ይገባል ብለዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ ህዝብም ለከፈለው መስዕዋትነት ተገቢውን ዋጋ ማግኘት አለበት።

ለዚህ ደግሞ አሳታፊ በሆነ መልኩ ከብሄርተኝነት የጸዱና አገር ወዳድ የሆኑ አስተዳዳሪዎች ሊኖሩ ይገባል ብለዋል።

ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የወጣበትን የአክሱም ኤርፖርት ጨምሮ በመንገዶች በድልድዮችና በሌሎችም መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም