የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በሰራተኞች በተፈጠረ ቅሬታ አገልግሎቱ መስተጓጎሉ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በሰራተኞች በተፈጠረ ቅሬታ አገልግሎቱ መስተጓጎሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ ሀምሌ 11/2010 የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በሰራተኞች ጥቅማጥቅም ጥያቄ ምክንያት ዛሬ አገልግሎቱ መስተጓጎሉ ተገለጸ። የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ የትራንስፖስርት አገልግሎቱ መስተጓጎሉን አረጋግጠዋል። "አገልግሎቱ የተቋረጠው ሰራተኞች ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ ባደረጉት የሥራ ማቆም አድማ መሆኑን ነው" አቶ ደረጀ የተናገሩት። ሠራተኞቹ ከካፍቴሪያ የምግብ አገልግሎት ዋጋ፣ ከአበል፣ የትርፍ ሠዓት ክፍያ የደመወዝ ጭማሪና ከመኖሪያ ቤት ጋር በተያያዘ ጥያቄ አንስተዋል ብለዋል። በመሆኑም በሁለቱም መስመሮች ላይ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ባይቋረጥም መመደብ የነበረባቸው ሰራተኞችና ባቡሮች በቁጥር ጎድለዋል ብለዋል። ጥያቄዎችንም ከግምት በማስገባት የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች ከሰራተኛው ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውንና ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ነው የጠቀሱት። አቶ ደረጀ አክለውም ተቋሙ በአፈጣኝ ችግሮቹን ፈቶ ወደ ሥራ እንደሚገባም አረጋግጠዋል። የሰራተኞች ተወካይ አቶ ዳዊት በላቸውም ተቋሙ ከሠራተኛው ጋር ሥምምነት መድረሱንና ጥቅማ ጥቅሞችን በማስከበር መስማማታቸውን ጠቅሰው መደበኛ ስራቸውን መቀጠላቸውንም ገልጸዋል።