ቀጥታ፡

የማይካድራ የንጹሃን ዜጎች ጭፍጨፋ የግፍና የጭካኔ ወንጀል ነው --ኢሰመኮ

አዲስ አበባ ህዳር 15/2013 (ኢዜአ) የማይካድራ የንጹሀን ዜጎች ጭፍጨፋ የግፍና የጭካኔ ወንጀል መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ የተጎዱትን ማቋቋም እና አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ ይገባል ብሏል። 

በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን በምትገኘው የማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅቱ በስልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን ጥቃት መፈጸሙን ኮሚሽኑ ገልጿል።

የተፈጸመው ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በንፁሃን ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል ነው ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ከሕዳር 5 እስከ ሕዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በማይካድራ ከተማ እንዲሁም በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጐንደር ከተማ ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ የደረሰበትን ግኝት የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

ይህ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ነው ብሏል ኮሚሽኑ በመግለጫው።

በመሆኑም ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ የሚያቀርብ መሆኑን አሳውቋል፡፡

በቀዳሚ ሪፖርቱ እንደተመለከተው በአካባቢው የነበረው የሚሊሻና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር በፌዴራሉ አገር መከላከያ ሰራዊት እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበር በተለይ ‹‹አማሮችና ወልቃይቴዎች›› ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪ ሲቪል ሰዎች ቤት ለቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ በገመድ በማነቅ፣ በስለት በመጥረቢያ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል፣ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ እንዲሁም ንብረት አውድመዋል" ይላል መግለጫው፡፡

ኢሰመኮ ከአካባቢው ምንጮች እስከ አሁን በአገኘው መረጃ በአነስተኛ ግምት እስከ 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥም እንደሚችል በሪፖርቱ መገለጹን ኢሰመኮ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ሳምሪ የሚባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጆች የሆኑ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሲቪል ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያን እና በእርሻ ቦታ ደብቀው በመሸሸግ ሕይወታቸውን እንዳተረፉላቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ምስክሮች አረጋግጠዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ‹‹በማይካድራ ከተማ በአነስተኛ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ እጅግ ዘግናኝ ኢሰብዓዊ ወንጀል ልብ ሰባሪ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያዊያን በብሔር ሳይለያዩ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሆነው መታየታቸው ልብ ይጠግናል፤ ስለ ወደፊት በሰላም አብሮ መኖርም ተስፋ ይሰጣል›› ብለዋል፡፡

አክለውም ‹‹የተጐዱ ሰዎችን እና አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋምና ከመጠገን በተጨማሪ፤ በዚህ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም