የደቡብ ክልል ለኦሎምፒክ ኮሚቴ የአምስት ሚሊዮን ብር ለመደገፍ ቃል ገባ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ክልል ለኦሎምፒክ ኮሚቴ የአምስት ሚሊዮን ብር ለመደገፍ ቃል ገባ
ሀዋሳ፣ ህዳር 15 /2013 (ኢዜአ ) የደቡብ ክልል ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ፡፡
የኦሎምፒክ ኮሚቴና የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ሃላፊዎች ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና ከሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር ዛሬ በሀዋሳ ተወያይተዋል፡፡
አቶ ርስቱ ይርዳው በወቅት እንደተናገሩት፤ የሀገሪቱን ስፖርት ዘርፍ ስምና ዝና ከፍ ለማድረግ በመደጋገፍ መሥራት ይጠይቃል፡፡
እንደ ሀገር ያለንን ትልቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም በኦሎምፒክ ስፖርት የምንሳተፍባቸውን ውድድሮች የተሳትፎ ዓይነቱን ማስፋት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ስፖርቱን የኢኮኖሚ ምንጭ፣የሠላም እና ለህዝብ ትስስር መጠቀሚያ ለማድረግ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የስፖርቱ ጉዳይ ከሠላምና ልማት ተነጥሎ ሊታይ አይገባም ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ዘርፉ ትውልድን የሚቀርጽ ፣አብሮነትንና ወንድማማችነትን የሚያጎለብት በመሆኑ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት እንደሰጠው ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የስፖርት መሰረት ልማትን በማስፋፋትና ዘርፉ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ ክልሉ በየደረጃው የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ክልሉ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚደንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው እንደ ሀገር በአንዳንድ የስፖርት ዓይነቶች ጥሩ ውጤት እየመጣ ቢሆንም የውድድር ስፖርት ዓይነቶችን በማስፋት ረገድ ውስንነቶች አሉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ መስራች ሆና ሳለ በአፍሪካ መድረክ በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ በስፋት መሳተፍ አለመቻሉ ከትኩረት ማነስ የመጣ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ከአትሌቲክስ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ጥሩ ተስፋ እየታየባቸው በሚገኙ ቴኳንዶ፣ብስክሌት እና ቦክስ ስፖርቶች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ዶክተር አሸብር ገልጸዋል፡፡
የኦሎምፒክ ኮሚቴው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ለተራዘመው የቶኪዮ 2021 ኦሎምፒክ አለም አቀፍ ውድድር የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ዶክተር አሸብር የደቡብ ክልል ለኮሚቴው ቃል ለገባው ድጋፍም አመስግነዋል ።