ቀጥታ፡

በሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች የጥፋት ተልዕኮ እንዳላቸው የተጠረጠሩ 77 ግለሰቦች ተያዙ

ወልድያ/ ደሴ/ ህዳር 15 /2013(ኢዜአ) በሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች የጥፋት ተልዕኮ እንዳላቸው የተጠረጠሩ 77 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ተገለጸ።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 52 በሰሜን ወሎ ወልድያ እና ቆቦ ከተሞች ቀሪዎቹ በደቡብ ወሎ ዞን እንደተያዙ ተመልክቷል።

የሰሜን ወሎ ዞን ሰላምና የሕዝብ ደህንነት መምሪያ ሃላፊ ኮሎኔል ሃይለ ማርያም አምባየ ለኢዜአ እንዳሉት በወልድያ እና ቆቦ የተያዙት ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ በአንድ ባንክ ብቻ እያንዳንዳቸው እስከ 600 ሺህ ብር ተቀማጭ ገንዘብ እንዳላቸው ተረጋግጧል።

ከመካከላቸውም ሁለቱ የመከላከያ አባል የነበሩ ኮሎኔሎች እንደሚገኙባቸው አመልክተዋል።

በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን ከህወሓት የጥፋት ተልዕኮ በመቀበል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ የወንጀል መከላከል ዋና ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ያለለት ዘገየ አስታውቀዋል።

ተጠርጣሪዎች ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ዜግነት ያላቸው ጭምር እንደሆኑ ጠቁመው ዶላር፣ የኢትዮጵያ ብር፣ የተለያየ የባንክ ሂሳብ ደብተሮች እና መታወቂያ እንደተገኘባቸው ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹን መያዝ የተቻለው በህብረተሰቡ ጥቆማና በጸጥታ ኃይሉ ክትትል መሆኑን የተናገሩት ኮማንደሩ ለህግ ለማቅረብም ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የመውጫና መግቢያ በሮች ተለይተው ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዞኑ ኮምቦልቻ ከተማ የቀበሌ አምስት ነዋሪ አቶ መሃመድ ሐሰን በሰጡት አስተያየት ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅተው የአካባቢያቸውን ሰላም ቀን ከሌት እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከተማዋ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት አካባቢ በመሆኗ አጠራጣሪ ጉዳይ ሲገጥመንና ጸጉረ ልውጥ ሰዎችን ስናገኝ ለህግ አካላት በማቅረብ እንዲያጣሩ የበኩላችንን እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም