ጁንታው ህዝቡን ወደ ጥፋት ከመውሰድ በተሰጠው የጊዜ ገደብ እጁን በሠላም እንዲሰጥ ተወላጆች ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
ጁንታው ህዝቡን ወደ ጥፋት ከመውሰድ በተሰጠው የጊዜ ገደብ እጁን በሠላም እንዲሰጥ ተወላጆች ጠየቁ

ሀዋሳ ህዳር 15/2013 (ኢዜአ) የህውሃት ጁንታ በተሰጠው የጊዜ ገደብ እጁን ለመንግስት በሠላም በመስጠት ህዝቡን ወደ ጥፋት ከመውሰድ እንዲቆጠብ በሀዋሳ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጠየቁ፡፡
ተወላጆቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ክልሉን ወደ ሠላሙ ለመመለስ የተቋቋመው ጊዜያዊ መንግስት የሚያከናውናቸው ተግባራት እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ዓለም መብራቱ እንዳሉተ በሀዋሳ ከተማ ከ35 ዓመታት በላይ በግል እና መንግስት ተቋማት ተቀጥረው ሲሰሩ ኖረዋል።
በኢትዮጵያ ሠላምና ልማት ሊኖር የቻለው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌላው ጸጥታ ሃይሉ በሚከፍለው መስዋዕትነት መሆኑን ኢትዮጵያዊያን በተለይም የትግራይ ህዝብ ይበልጥ እንደሚገነዘብ አስረድተዋል፡፡
ህወሓት ግን ሀገርንና ህዝብን በመካድ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት የሚወገዝና በማይረሳ የታሪክ መዝገብ የሚጻፍ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው መንግስት ለህዝብ ደህንነት የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
የትግራይ ህዝብን መሸሸጊያ አድርጎ ለችግር ያጋለጠው የህወሃት የጥፋት ቡድንን ሥርዓት ለማሲያዝ በመንግስት እየተካሄደ ያለው ህግ የማስከበር እርምጃ መፍጠን እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ የተመኘውን ልማትና ሠላም የሚያገኝበት ጊዜ እንዲፋጥን አዲስ ለተቋቋመው ጊዜያዊ መንግስት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
አቶ ነጋሽ አጽባህ በበኩላቸው ህወሃት በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው አስጸያፊ ድርጊት ሃገርን ለወራሪ ያጋለጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ህወሃት ክልሉን በመራባቸው ዓመታት ህዝብ በድህነት እንዲማቅቅ ያደረገው ህገወጥ ቡድን እንደሆነ መላው የትግራይ ህዝብ እንደሚያውቅም ጠቁመዋል።
ጁንታው የቸገረው በህገወጥ መንገድ የዘረፈውና የሰበሰበው ሃብት እንጂ የትግራይ ህዝብ ጉዳይ አስጨንቆት እንዳልሆነ ሁሉም ገብቶታል ብለዋል፡፡
ጁንታው በተሰጠው የጊዜ ገደብ እጁን ለመንግስት በሠላም በመስጠት ህዝቡን ወደ ጥፋት ከመውሰድ እንዲቆጠብም ጠይቀዋል።
በመላው ኢትዮጵያ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ከተቋቋመው ጊዜያዊ መንግስት ጎን በመሆን ህዝቡ የተጠማውን ሠላም ለመመለስ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
እሳቸውም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
ቡድኑ በሌሎች መስዋዕትነት መራመድ የለመደ ነው ያሉት አቶ ነጋሽ በተለይ የትግራይ ወጣት በእነዚህ ክፉዎች ሴራ ለእሳት ከመማገድ ቆም ብሎ ማሰብ እንዳለበትም ጠቁመዋል።