ቀጥታ፡

ለአገር መከላከያ ሠራዊት 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተበረከተ

አዲስ አበባ ህዳር 15/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተቋማት፣ ከማኅበራትና ከግለሰቦች በሕግ ማስከበር ተግባር ላይ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ ቀጥሏል። 

የኢትዮጵያ ቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማኅበርና ጤና ዘይት ፋብሪካ ግምቱ 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የሆነ ሰንጋና የምግብ ዘይት ድጋፍ አበርክተዋል።

የኢትዮጵያ ቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማኅበር 153 ሰንጋዎች፤ ጤና ዘይት ፋብሪካ ደግሞ 2 ሺህ ሊትር ዘይት ነው ያበረከቱት።

"የሕዝብ ልጅ ለሆነው መከላከያ ሠራዊት የምናደርገው ድጋፍ ይቀጥላል" ያሉት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሞገስ ኃይሌ የአዲስ አበባ ቄራ ገበያ ነጋዴዎች 60፣ የሸጎሌ ገበያ ነጋዴዎች 42፣ የአቃቂ ገበያ ነጋዴዎች 33 እንዲሁም የካራ አሎ ነጋዴዎች 18 ሰንጋዎችን መስጠታቸውን ገልጸዋል።

ጤና ዘይት ፋብሪካ የለገሰው ሁለት ሺህ ሊትር ዘይትም 121 ሺህ ብር ግምት እንዳለው ተገልጿል።

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሐብታሙ ጥላሁን ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፣የሕዝብ ድጋፍ ለሠራዊቱ ጀግንነትና አሸናፊነት ስንቅ መሆኑን ገልፀዋል።

"ድጋፉ ሠራዊቱ በትልቅ የሞራልና የአሸናፊነት መንፈስ እንዲገሰግስ የኋላ ደጀን ሆኖታል" ብለዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ የመዲናዋ ነዋሪ ሕዝብ አንድነቱን ለሚያስጠብቅለትን ሠራዊት በመደገፍ አጋርነቱን እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕዝቡ ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በሠራዊቱ ላይ በፈፀመው ጥቃት በቁጭት ተነሳስቶ እያደረገ ያለው ድጋፍ አኩሪ መሆኑንም አክለዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም