ቀጥታ፡

ለህወሓት ጁንታ የተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ የመንግሥትን ትዕግሥትና ሆደ-ሰፊነት ያሳያል - የመዲናዋ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ህዳር 15/2013 (ኢዜአ) ለህወሓት ቡድን የተሰጠው የሶስት ቀናት በሠላም እጅ የመስጠት ጥሪ የመንግሥትን ትዕግሥትና ሆደ-ሰፊነት እንደሚያሳይ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

መንግሥት ለህወሃት ጁንታ የሰጠው የ72 ሰዓታት እጅ የመስጠት ጊዜ የሚደነቅ፣ ትዕግሥቱንና አስተዋይነቱንም የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሕገ-ወጡ ቡድን ያሰማራቸው አባላት በሠላማዊ መንገድ እጃቸውን እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

ምንም እንኳን ሕገ-ወጡ ቡድን በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት አሳዛኝ ቢሆንም፤ መንግሥት ለወንጀለኞቹ ያቀረበውን ሠላማዊ ጥሪ መቀበል እንዳለባቸው ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።

አቶ ታፈሰ ወጋየሁ ቡድኑ ከዚህ ቀደም መንግሥት የሰጠውን ዕድል እንዳልተጠቀመበት አስታውሰው፤ “ለሕዝባቸው የሚያስቡ ከሆነ የመጨረሻ ዕድላቸውን ይጠቀሙበት” ብለዋል።

ወጣት ዳንኤል መኮንን በበኩሉ ይህ ቡድን በአገር አለኝታው ሠራዊት ላይ ወንጀል የፈጸመው የጁንታ ቡድን መንግሥት የሰጠውን ተጨማሪ ጊዜ እንዲጠቀምበት መክሯል።

አጥፊው ቡድን ሌላ ተጨማሪ ጥፋት ሳያስከትል ራሱን ለመንግሥት አሳልፎ መስጠት እንዳለበት የገለጸችው ደግሞ ዮርዳኖስ እስማኤል ነች።

መምህር ነቢያት መኮንን ለዓመታት “በሕዝብ ውስጥ ተደብቆ የሥልጣን ጥሙን ለማርካት ሲሰራ የቆየው ቡድን ከመከላከያ ሠራዊቱ ሊያመልጥ ስለማይችል በፍጥነት እጁን ሊሰጥ ይገባል” ብለዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ የጁንታው አባላት የመንግሥትን ሠላማዊ ጥሪ በመቀበል እጃቸውን በአስቸኳይ እንዲሰጡም ምክራቸውን ለግሰዋል።

ህወሓት ያሰማራቸው ታጣቂዎችም ራሳቸውንና ሕዝባቸውን ለማዳን መንግሥት የሰጠውን ጊዜ እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል።

የትግራይ ሕዝብ በተለይም የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች የህገ-ወጡ ቡድን አባላት የተደበቁባቸውን ቦታዎች በማጋለጥና በመጠቆም ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል።

“በዚህም ተጨማሪ የሕይወትና የንብረት ውድመትን ማስቀረት ይቻላል” ነው ያሉት።

የትግራይ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ከሕግ አስከባሪው ሠራዊት ጎን በመቆም ሕገ-ወጡን የህወሓትን ጽንፈኛ ቡድን አሳልፎ እንዲሰጥም መክረዋል።

መንግስት የሰጠውን የ72 ሠዓት እጅ የመስጫ ተጨማሪ ጊዜ ጥሪ ተከትሎ በርካታ የትግራይ ሚሊሺያና ልዩ ኃይል አባላት በየግንባሩ እጃቸውን በመስጠት ላይ መሆናቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም