ቀጥታ፡

ከሙያዊ ስነ-ምግባር ያፈነገጠ የውጭ ጣልቃ ገቦች ጥብቅና

በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ካምፕ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ “የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል፤ ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል።” በማለት ነበርየኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድለሠራዊቱመመሪያ ያስተላለፉት።

በትግራይ ክልል የመሸገው የህወሃት ቡድን በተለያዩ ጊዜያት በክልሉ ሚዲያዎች በኩል በሚሰጣቸው መግለጫዎች ሀገሪቱ ልትበታተን እንደምትችል ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል። አልተሳካለትም እንጂ፤ ዓላማውን ለማሳካት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አለመረጋጋት እንዲከሰት ብዙ ጥረት አድርጓል። በመጨረሻም በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እስከመሰንዘር ደርሷል። ከጥቃቱ አንድ ቀን አስቀድሞ የህወሃት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለክልሉ ሚዲያ በሰጡት መግለጫ “ሰራዊታችንን አዘጋጅተናል፤ ሚሊሻችንን አዘጋጅተናል፤ ልዩ ኃይላችንን አዘጋጅተናል። ጦርነት ለማስቀረት ነው የተዘጋጀነው። መዋጋት ካለብን ግን፤ ድል ለማድረግ ተዘጋጅተናል" ሲሉ ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ። የሀገራት መሪዎችም በመከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ የውጭ አገራት ተንታኞች እውነታውን ወደ ጎን በመተው በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ለፈጸመው ቡድን ጥብቅና በመቆም መሟገትን ተያይዘዋል። እነዚህ ተንታኞች እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት ቢችሉ ባልከፋም ነበር፤ ችግሩ ጥፋትን በጥፋት ለማካካስ መንቀሳቀሳቸው ነው እንጂ።    

በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ዙሪያ ትንታኔ ከሚጽፉት መካከል ማርቲን ፕላውት አንዱ ነው። ማርቲን ፕላውት ምስራቅ አፍሪካን በተለይም ኢትዮጵያን፣ ሰሜናዊ ሱዳንና ኤርትራን እንዲሁም ጅቡቲን የእጃቸው መዳፍ ያህል አብጠርጥሮ እንደሚያውቅ የሚነገርለት ሲሆን በርካታ አስተያየት ሰጪዎች የህወሃትን የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ የነደፈ ታጣቂ ቡድኑን ለምእራቡ አለም ይበልጥ ያስተዋወቀ ስለመሆኑ ህወሃት ያሳተማቸው ሰነዶች ምስክሮች ናቸው።

ጋዜጠኛ ፕላውት እኤአ በ1950 ደቡብ አፍሪካ ተወልዶ እንግሊዛዊ ዜግነት ያለው ሲሆን፤ ከ1984 ጀምሮ በቢቢሲ የዜና ተቋም የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ውስጥ ከጀማሪ ሪፖርተር እስከ ክፍሉ ዋና ሃላፊነት ሲያገለግል ቆይቷል። በእንግሊዝ የውጭ ግንኙነትና የኮመን ዌልዝ ጉዳዮች ቢሮ እና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሆኖ ስለመስራቱ የሚነገርለት ማርቲን ፕላውት፤ በአሁኑ ወቅት የእንግሊዙ ሮያል የውጭ ግንኙነት ተቋም የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ተመራማሪ በመሆን እየሰራ ይገኛሉ። 

ማርቲን ፕላውት ከህወሃት ጋር ግንኙነት መፍጠሩ  የሚነገርለት በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ ጽሑፎችን ማውጣት መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። ማርቲን ፕላውት የሚያወጣቸው ዘገባዎች በአብዛኛው ሙያዊ ስነ ምግባርን የተከተሉ እንዳልነበሩ አንዳንዶች ይተቻሉ። አንድ ኤርትራዊ ጸሀፍት ማርቲን ፕላውትን “የፕሮፓጋንዳ አራማጅ የሆነው የምዕራባዊያኑ የሞት ወኪል” ሲል ይገልጻቸዋል።  

በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው ትታኔዎች በይዘታቸው ህወሃትን የሚያሞግሰው ፕላውት ከለውጡ ማግስት የተዛቡ ዘገባዎችን ሲያሰራጭእና የሴራ ፖለቲካውን ሲያንጸባርቅ ቆይቷል። ለዚህ ማሳያው ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የሰላም ስምምነት ማድረጓን ተከትሎ እዚያ አካባቢ ሰፍሮ የነበረው የመከላከያ ጦር ወደ መሀል አገር ሲንቀሳቀስ በመቃወም ጽፏል። ለዚህም “ትግራይ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከባድ መሣሪያዎችን ወደ ኦሮሚያ ለማንቀሳቀስ የተደረገውን ሙከራ እንዲቆም አድርጓል” ሲል ትንታኔ ሰርቷል።

መንግስት ህግን ለማስከበር እየወሰደ ባለው እርምጃ ዙሪያ ማርቲን ፕላውት በየእለቱ በትዊተር ገጹ ላይ ጉዳዩን ቀጠናዊ ለማስመሰል ጥረት ያደርጋል። በሌላ ጊዜ ደግሞ በመላው አገሪቱ ጦርነት እንደተቀሰቀሰ ይገልጻል። የህወሃት የጥፋት ቡድን አስመራ ላይ ያደረሰው የሮኬት ጥቃት አሜሪካ ያወገዘችበትን ሃሳብ ማርቲን ፕላውት ይቃወማል።

ኤርትራ ከዚህ በፊት ትግራይ ላይ ጥቃት ማድረሷን ዘንግተውት ነው? ሲል ይሞግታል።

የትግራይ ጦርነትን ያወሳሰቡ አራት ምክንያቶች በሚለው ጽሁፍ ላይ ህግ የማስከበሩን እንቅስቃሴ እንደ ሲቪል ጦርነት ከመቁጠሩም በላይ እንደምክንያት የዘረዘራቸው ነጥቦች ግለሰቡ ከህወሃት ቡድን ጋር ልዩ ትስስር እንዳለው ማሳያ ነው። በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቅላይነት መንፈስ “A quest for total control ፣ የአማራ ግዴለሽነትና መሬት አስመላሽነት (Amhara irredentism)፣ የጦርነቱ ሀሳባዊ ልኬቶች (Ideological dimensions of the war) እና የኢሳያስ አፈወርቂ በቀል (Afeworki’s vengeance) በሚል ፕሮፓጋንዳውን ሰንዝሯል።በዚህ ጹሁፍ እንደተገለጸው ህግ የማስከበር ዘመቻውን ቀጠናዊ ለማድረግ ከማሰቡም በላይ እሱና መሰሎቹ በሚፈልጉት መልኩ አገሪቷን ለመበታተን ያለመ ዘገባ ነው።

በሌለ በኩል ለኤርትራ እና ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ ለሆኑት ስህተቶች ለምን ትግራይን  ተጠያቂ ያደርጋል? በሚለው ጽሁፍ ላይ ደግሞ የህወሃትን ጥፋት ከመግለጽ ይልቅ ለምን እሱ ይወቀሳል ለምንስ ተጠያቂ ይደረጋል በሚል ሙያዊ ስነምግባርን በሳተ መልኩ ጥብቅና የቆመበት ዘገባ መሆኑ ግልጽ ነው። የትግራይ ቀውስ ‘እንዴት መዋጋት እንዳለባቸው ያውቃሉ እናም እስከ መጨረሻው ሊያደርጉት ይችላሉ’ በሚለው ትንታኔው ውስጥ በህወሃት ላይ እየተከናወነ ያለውን ህግ የማስከበር ተግባርን በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠር እንደሆነ በመግለጽ የለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ሊደርስ ይችላል ሲል ገልጿል።

ማርቲን ፕላውት በጽሑፉ ላይ ህወሃት ዘመቻውን መቀልበስ እንደምትችል የሀሳቡ መነሻ ያደረገ ሲሆን በሀተታው አንድም ቦታ ላይ በአገር መከላከያ ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን  አልጠቀሰም።  ግልሰቡ በጽሑፉም ሆነ በትዊተር ገጹ ላይ በሚጭናቸው መረጃዎች አንዴ ህወሃት ጦርነቱን ትቋቋመዋለች ይላል፤ ሲቀጥል ደግሞ የእርስ በርስ ጦርነት ሊቀሰቀስ ጫፍ ላይ ደርሳል ሌላ ጊዜ ደግሞ ውጊያው ቀጠናዊ ነው በማለት ይጽፋል፤ አለፍ ብሎም “ንጹሃን እያለቁ ነው” በማለት የጥብቅና እርምጃውን ቀጥሎበታል። 

የሀገር መከታ የሆነው መከላከያ ሰራዊት የደረሰበትን ጥቃት መክቶ ከመከላከል ተሻግሮ ህገ ወጡን ቡድን ለፍርድ ለማቅረብ ተቃርቧል።  ማርቲን ፕላውት እና መሰሎቹ ግን ለእውነትና ለፍትህ በመቆም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምሳሌ ከመሆን ይልቅ ለጥፋት ከሚሰራው ቡድን ጋር መተሳሰራቸው ታሪክ ይቅር የማይለው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም