ቀጥታ፡

"የህወሓት አስተዳደር የአገር ህልውናን አደጋ ላይ ከመጣል ባለፈ ህዝቡን በአግባቡ እንዳናገለግል አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሮብናል"... አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2013(ኢዜአ) ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኢትዮጵያን ባስተዳደረባቸው ዓመታት ዜጎች ከአገራቸው ክብር ይልቅ ለማንነታቸው እንዲጨነቁ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድር እንደነበር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ተናገሩ።

የየትኛውም አገር ዜጋ ስለአገሩ በኩራትና በክብር ሲናገር ኢትዮጵያዊያን በዘር ተከፋፍለው ''ኢትዮጵያዊ ነኝ'' ለማለት ድፍረት ያጡበት ዋነኛ ምክንያት ማንነት ከአገር እንዲጎላ በመደረጉ ነው ብለዋል። 

አምባሳደር አስፋው የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴን፣ የስኳር ልማት ኮርፖሬሽንን፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ልማት ድርጅትን ከሚኒስትርነት ጀምሮ በከፍተኛ የስራ ሃላፊነት አገልግለዋል።

ከዚህ ባለፈ በህንድ፣ በኩባና አካባቢዋ የኢትዮጵያ ባለ-ሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።

አምባሳደር አስፋው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ህወሓት አብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ስርዓትን ተገን በማድረግ በየቦታው የምስለኔ አስተዳዳሪዎችን በመሾም የበላይነቱን ለማስጠበቅ ሲሰራ ነበር ብለዋል። 

በህወሓት ሲቀነቀን የነበረው የማንነት ፖለቲካ የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ ከመጣል ባለፈ ከህወሓት አመራሮች ይሁንታ ውጪ የሚወሰን ውሳኔ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

በዚህ ምክንያት በተለይ በአመራርነት ያሉ ሰዎች ከማዕከል የሚመጡ ውሳኔዎችን ''ቢስማሙም ባይስማሙም ለውሳኔው ተገዥ የመሆን ግዴታ ይጣልባቸው ነበር'' ብለዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፣ ህወሓት የበላይነቱን አስጠብቆ ለማቆየት በአገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች የራሱን ሰዎች በመመደብ የእጅ አዙር አስተዳደር ሲያካሂድ ቆይቷል።

ለዚህም ሽፋን የሚሰጠው የአካባቢውን ተወላጅ ከፍተኛ የስራ ሃላፊነት ላይ ቢያስቀምጥም ውሳኔውን ግን የሚወስኑት በምስለኔ የተቀመጡ አስተዳዳሪዎቹ መሆናቸውን ለአብነት ያነሳሉ።

ህወሓት አብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ስርዓት ላይ ሙጥኝ ማለቱ የበላይነቱን አስጠብቆ ለማቆየት መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር አስፋው፤ ከእርሱ በላይ በፌዴራል ስርዓት ሽፋን አሃዳዊነትን ያቀነቀነ የለም ሲሉ ይመሰክራሉ።

ህወሓት ይህን የይስሙላ ስርዓት ለማስቀጠል የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደማይኖርም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ አንዱ ማሳያ ስርዓቱ ወደ ትክክለኛ መስመር ሲገባ የአገሪቱን ሰላም በማደፍረስ የንጹሃን ዜጎች ህይወት እንዲጠፋ እያደረገ ነው ብለዋል። 

የትኛውም አገር ያለ ዜጋ ስለአገሩ በኩራትና በክብር ሲናገር ኢትዮጵያዊያን በዘር ተከፋፍለው ''ኢትዮጵያዊ ነኝ'' ለማለት ድፍረት ያጡበት ዋነኛ ምክንያት ማንነት ከአገር እንዲጎላ በመደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

‘‘የህወሓት አስተዳደር የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ ከመክተት ባለፈ ህዝቡን በአግባቡ እንዳናገለግል አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል’’ ነው ያሉት አምባሳደር አስፋው።

''በጥቂት የፖለቲካ አመራሮች ስህተት የአገር ክብር ከማንነት በታች ሲሆን ማየት በጣም ያሳፍራል''ያሉት አምባሳደሩ፤ በእርሳቸው የስራ ሃላፊነት ዘመን የአገር ህልውና አደጋ ላይ በመውደቁ ጸጸት እንደሚሰማቸውም ነው የገለጹት። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም