ህወሓትን መቃወም ወይም ጨቆነን ማለት በሽብር ያስከስሳል፤ ያስገድላል -- እጅ የሰጡ ሚሊሺያዎች - ኢዜአ አማርኛ
ህወሓትን መቃወም ወይም ጨቆነን ማለት በሽብር ያስከስሳል፤ ያስገድላል -- እጅ የሰጡ ሚሊሺያዎች
አዲስ አበባ ህዳር 14/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ህወሓትን መቃወም ወይም ተጨቆንን ማለት በሽብር እንደሚያስከስስ ካልሆነም እንደሚያስገድል እጃቸውን ለመከላከያ ሠራዊት የሰጡ የክልሉ ሚሊሺያዎች ተናገሩ።
ከሐዝቡ ጋር አንበጣ ሲከላከሉ የዋሉትን የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሌሊት ከፈጇቸው በኋላ ይሄ የትግራይ ክልል መንግስት ሰው በላ ነው ብለን ሸሽተናል ነው ያሉት።
ህወሓት ቢጨቁነንም ጨቆነን ብለን አናወራም፤ ምክንያቱም አሸባሪ ብሎ ስለሚያስገድለን ያሉት ሚሊሺያዎቹ ዘራፊው የህወሓት ቡድን የግል ፍላጎቱንና ጥቅሙን ለማስጠበቅ የትግራይ ወጣቶችን ለጦርነት እየማገደ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሚሊሺያዎቹ ከትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ስልጠና ሳይሰጣቸውና ከማን ጋር እንደሚዋጉ እንኳን ሳይነገራቸው በድንገት መዝመታቸውን ለኢዜአ ገልፀዋል።
"መንግሥት የለም ተዋግተን መንግሥት እንመሰርታለን" ከሚለው ዲስኩር ባለፈ ከትግራይ አርሶ አደር ጋር አንበጣ የተከላከለውን ሠራዊት በሌሊት የሚወጋ ሰው በላ ቡድን እንደማይራራልን ተረዳን ይላሉ።
በማያውቁት ሁኔታ፣ ባልሰለጠኑበት ሙያ ተገደው ወደ ጦር ግንባር መዝመት ያልተዋጠላቸው ሚሊሺያዎች ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በዱር በገደል ሲንከራተቱ ቆይተው ትጥቃቸውን በማስረከብ እጅ ሰጥተዋል።
በትግራይ ክልል ከህወሓት ጀሌዎች ሃሳብ ውጭ ሌላ ሀሳብ ወይንም ልዩነትን ማንፀባረቅ በሽብር የሚያስጠይቅ ወንጀል ተደርጎ ስለመቆየቱም ገልፀዋል።
አሁንም ወደ ጦር ግንባር ዝመቱ ከተባሉ በኋላ በቀን አንድ ዳቦ ማግኘት ዕድለኝነት ነው ይላሉ ሚሊሺያዎቹ።
'የማትዘምቱ ከሆነ እኛ እንገድላችኋለን' የሚል ማስፈራሪያ የደረሰባቸውና እጃቸውን ለመከላከያ ሠራዊት የሰጡ የትግራይ ክልል ሚሊሺያዎች 'ኑሮ ፈተና ሆኖብናል፣ ነፃነት ተነፍጎናል' ነው ያሉት።
እንዳንሰደድ ልጆቻችን፤ እንዳንኖር ወከባና አፈናው መድረሻ አሳጥቶናል፤ መንግሥት ሊደርስልን ይገባልም ብለዋል።
መንግሥት ይገድላችኋል በሚል የተሳሳተ መረጃ በዱር በገደል የሚንከራተቱ የትግራይ ወጣቶች እጃቸውን ሰጥተው በሠላም እንዲኖሩም መክረዋል።
ፅንፈኛው ቡድን ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የትግራይ ጠላቶች እንደሆኑ አድርጎ በመስበክ ሕዝቡን እያሳሳተ መሆኑንም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ አንድ አገር በመሆኗ እኛም በወያኔ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ አንዋጋም ብለናል፤ ሌሎችም እጃችሁን ስጡ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።