ህዝቦችን ሲያጋጭ የኖረን የህወሓት የጥፋት ቡድን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ ወጣቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝቦችን ሲያጋጭ የኖረን የህወሓት የጥፋት ቡድን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ ወጣቶች ገለጹ
ባህርዳር፤ ህዳር 14/13 (ኢዜአ) የህወሃት የጥፋት ቡድን የግል ፍላጎቱን ለማሳካት የኢትዮጵያዊያንን አንድነት በመጻረር እርስ በርስ ሲያጋጭ የኖረ የህዝብ ጠላት በመሆኑ ቡድኑን ስርዓት ለማስያዝ የሚወሰደውን እርምጃ እንደሚደግፉ ወጣቶች ተናገሩ።
የአማራ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ኃይለሚካኤል ካሳሁን ለኢዜአ እንደተናገረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገሩን ዳር ድንበር ከማስከበር ባለፈ ለወገኑ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ በመጠበቅ ጋሻና መከታ ነው።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ጥቃትና ክህደት ተወልዶ ያደገበት የሴራ ፖለቲካው ማሳያ መሆኑን ጠቅሷል።
የቡድኑ አባላት የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይረጋገጥ፣ ልማት እንዲደናቀፍ፣ ህዝቦች በአንድነት እንዳይኖሩ እርስ በእርስ ሲያጋጩ የኖሩ ጠላቶች እንደሆኑም ገልጿል።
ቡድኑ ለዘመናት በኢትዮጵያዊያን ላይ ያደረሰው ጉዳት ሳይፀፅተው በህዝብ ዘንድ ያጣውን ተቀባይነት በጉልበት ስልጣኑን ለማራዘም ባልተጠበቀ ሰዓት የፈፀመው አስነዋሪ ተግባር የሚያቆጣ ነው ብሏል።
በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለውን ህግን የማስከበር እርምጃ ከሠራዊቱ ጎን በመሆን የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ጠቅሶ፤ የደም ልገሳ ስራ መጀመራቸውን ተናግሯል።
''በዘራፊው ቡድን ሴራ ሃገር እንድትተራመስ አንፈቅድም፤ ለዚህም አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን'' ብሏል።
ከትግራይን ህዝብ ጎን በመሆን ሰብል በመሰብሰብና አንበጣ በመከላከል አጋርነቱን በተጨባጭ ላሳየው ሠራዊት ከሃዲው ቡድን የፈፀመው ጥቃት አሳፋሪ ነው ያለው ደግሞ የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ዘላለም ታከለ ነው።
ከ20 ዓመታት በላይ በበረሃ ጉድጓድ ቆፍሮ፣ ድንጋይ ተንተርሶ፣ ሃሩርና ቁር ሳይበግረው ህዝቡንና ሀገርን ሲጠብቅ የኖረን ሠራዊት በዚህ መልኩ ማጥቃት ከውጭ ወራሪ ጠላት በላይ መሆኑን ያሳያል ሲልም ጠቅሷል።
ከሀዲውን ቡድን ሥርዓት ለማሲያዝ መንግስት የጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል።
የባህርዳር ከተማ ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት በላይነህ ደጉ በበኩሉ አጥፊው የህወሓት ቡድን ያለፉትን ዓመታት በህዝብና ሀገር ላይ ያደረሰው ጉዳት አልበቃው ብሎት ዛሬም በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ዘግናኝ ድርጊት በታሪክ ይቅር የማይባል ነው ብሏል።
ቡድኑ የሀገሪቱን ክልሎች ለማተራመስ በርካታ አሸባሪዎችን አሰልጥኖ ያሰማራ በሆኑ በተለይ ወጣቱ ነቅቶ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት እንዲጠብቅ የማህበራቸው አባላት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑንም ተናግሯል።
የትግራይ ህዝብ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ በማድረግ አሸባሪው ቡድን ለህግ እስኪቀርብ ህግን ለማስከበር እየተወሰደ ያለው እርምጃ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያለችው ደግሞ ወጣት አይሻ ወርቁ ናት።