የአዲስ አበባ ሴቶች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ያዘጋጁትን ስንቅ አስረከቡ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ሴቶች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ያዘጋጁትን ስንቅ አስረከቡ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/2013(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ሴቶች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ያዘጋጁትን ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ስንቅ ለመከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ አስረከቡ፡፡
ስንቁን የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ፣ የከተማዋ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮና የሴቶች ማኀበር ኃላፊዎች በምድር ኃይል ግቢ በመገኘት አስረክበዋል ፡፡
የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሐዲስ ኪዱ ሴቶች የሕግ ማስከበሩ ተግባር ከተጀመረ አንስቶ በተለያዩ መንገዶች ከሠራዊቱ ጎን መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሂደቱ በድል እስኪጠናቀቅም የሴቶች ተሳትፎ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
የመዲናዋ ሴቶች ሠራዊቱን ለመደገፍ ስንቅ ማዘጋጀታቸውን የገለጹት የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መልዓኬ ዓለማየሁም ስንቁ በሶ፣ ዳቦቆሎ፣ በርበሬ፣ ዱቄት፣ ድርቆሽና ሌሎችም ምግቦችን ማካተቱን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ታዘዘ ደግሞ 'ሴቶች በሕግ ማስከበር ሂደቱ እኩል ተሳታፊዎች ነን' ብለዋል፡፡
ስንቁን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ ለተበረከተው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ የሕግ ማስከበር ሂደቱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ የሴቶች አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የትግራይ ክልል ሴቶችም የሕግ ማስከበር ዘመቻውን በመደገፍ ከመንግሥት ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።
በሕግና በአገር ሕልውና ማስከበር ላይ ለሚገኘው ሠራዊት እየተደረገ ያለው የተለያየ ድጋፍ አሁንም እንደቀጠለ ነው።