አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እና ፋሲል ከተማ ተለያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እና ፋሲል ከተማ ተለያዩ
አዲስ አበባ ሃምሌ 11/2010 የኮንትራት ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ ጋር ተለያየ። ፋሲል ከተማ በውጤት ማጣት ምክንያት አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ እና ምክትሉን ተገኝ እቁባይን ካሰነበተ በኋላ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን አሰልጣኝ አድርጎ መቅጠሩ የሚታወስ ነው። ከክለቡ ጋር የገባው ውል ከመጋቢት እስከ ሰኔ መጨረሻ 2010 ዓ.ም ድረስ እንደነበር አሰልጣኝ መሳይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጿል። ስምምነቱ እሱ ክለቡን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ያሉ 12 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች እንዲያሰልጥን መሆኑንና ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም በአርባምንጭ ስታዲየም ከአርባምንጭ ከተማ በተደረገው የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ መጠናቀቁን አስታውቋል። ፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ በቀጣይ ውል ማራዘምን አስመልክቶ ያቀረበው ሀሳብ ባለመኖሩና በኮንትራቱ መሰረት ክለቡ ከእርሱ ጋር ያለውን ቆይታ ማቆም በመፈለጉ ከክለቡ መለያየቱን አስታውቋል። አሰልጣኝ መሳይ እስካሁን ከሌላ ክለብ ጋር ምንም አይነት ድርድር እንዳልጀመረ፤ ሆኖም በቅርቡ ወደ አሰልጣኝነት እመለሳለሁ ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል። ፋሲል ከተማ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 40 ነጥብ በመሰብሰብ ሰባተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።