ቀጥታ፡

የህወሃት ቡድን በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚያስጠይቁ ተግባራትን ፈፅሟል- የዘርፉ ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/2013 (ኢዜአ) የህወሃት ፅንፈኛ ቡድን በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚያስጠይቁ ተግባራትን መፈፀሙን የሰብአዊ መብትና የህግ ምሁራን ተናገሩ። 

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሰብዓዊ መብትና የህግ ምሁራን የህወሃት ቡድን በኢትዮጵያ የፈፀመው አረመኔያዊ ተግባር በአለም አቀፍ ህግ በጦር ወንጀለኝነት ተጠያቂ የሚያደርገው ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ዳይሬክተር መስኡድ ገበየሁ እንደሚሉት ህጻናትን ለውጊያ መልምሎ ማሰለፍ በዓለም አቀፍ ህግ ያስጠይቃል።

በዓለም አቀፍ ህግም ይሁን ኢትዮጵያ ፈርማ በተቀበለቻቸው ኮንቬንሽኖች ህፃናትን ለውትድርና ማሰለፍ በወንጀል ተጠያቂ ያደርጋል ብለዋል።

የህወሃት ቡድን ግን እነዚህን ድንጋጌዎች በመጣስ ታዳጊ ህፃናትን ለውጊያ ማሰለፉ የሚታወቅ ነው።

ከዚህ ባለፈም የህወሃት ቡድን ሰላማዊ ዜጎችን ሆን ብሎ በጅምላ በመግደል በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚያስጠይቅ ድርጊት መፈፀሙን ገልጸዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የፖሊሲና አመራር መምህርና ተመራማሪ አለማየሁ ደበበ እንደሚሉትም ቡድኑ የህጻናትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመጣስ የፈጸማቸው ድርጊቶች በአለም አቀፉ የጦር ወንጀለኝነት ያስጠይቀዋል።

የህግ ባለሙያው አቶ መልካሙ አጎ በኢትዮጵያ ህግ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ እንደ ወንጀሉ አይነት ከሞት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት የሚያደርስ ቅጣት ይጥላል ይላሉ።

የህወሃት ቡድን የአገር ክብርና መከታ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት አባላትና በንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰው ጥቃትም ከባድ ወንጀል መሆኑን አብራርተዋል።

የወንጀል ድርጊቱ ከኢትዮጵያ አልፎ በአለም አቀፍ ህግ የሚያስጠይቅ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ዳይሬክተር መስኡድ ገበየሁ መንግስት አሁን እያካሄደ ያለው የህግ ማስከበር ዘመቻ አንዱ ዓላማ ህጻናትን ወደ ጦርነት የሚማግዱ ወንጀለኞችን ተጠያቂ ማድረግ ነው ብለዋል።

ህገ ወጡ ቡድን ህጻናትን ጨምሮ በአገሪቷ ላይ ላደረሰው ሰብአዊ ጉዳት በህግ ተጠያቂ እንደሚደረግም ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።

የህወሃት ቡድን ሰላማዊ ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ከመግደል በተጨማሪ መሰረተ ልማቶችን በማውደም በኢትዮጵያ አስነዋሪ ተግባር መፈፀሙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም