ቀጥታ፡

ህግ የማስከበር እርምጃው ከትግራይ ህዝብ ጋር ያለንን አብሮነትና ትስስር ያጠናክራል- የጎፋ ዞን ነዋሪዎች

ሀዋሳ፣ ህዳር 13/2013 ( ኢዜአ ) መቀሌ በመሸገው ከሀዲው የህወሀት ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው ህግ የማስከበር እርምጃ ከትግራይ ህዝብ ጋር ያለንን ትስሰር የሚያጠናክር ነው ሲሉ የጎፋ ዞን ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ 

የህወሀት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የወሰደው ጥቃት የሀገር ክህደት መሆኑን ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የጎፋ ዞን ነዋሪዎች መካከል አቶ ተክለማርያም ፍቅሬ በሰጡት አስተያየት መከላከያ ሰራዊት ከሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች ተውጣጥቶ የተገነባ እንጂ የህወሀት አመራሮች እንደሚያራግቡት የማደናገሪያ ወሬ ለአንድ ፓርቲ የወገነ አይደለም ።

"ቡድኑ ላለፉት 27 ዓመት የሀገሪቱን ሥልጣን ተቆጣጥሮ  በነበረበት ወቅት ሰራዊቱን ከህዝባዊነት ይልቅ የአንድ ፓርቲ አገልጋይ አድርጎ ለመቅረፅ ሲጥር በመቆየቱ የራሱን አመለካከት ለማደናገሪያነት እየተጠቀመበት ነው" ብለዋል።

"የህወሀት ቡድን የህዝብ ልጅ በሆነው መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙ እጅግ አስቆጥቶናል" ያሉት አቶ ተክለማርያም ድርጊቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ተደርጎ የማይታወቅ የሀገር ክህደት መሆኑን ገልጸዋል።

"የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ ኢትዮጵዊያንን ያስቆጣው በመቀሌ የመሸገው ፅንፈኛው የህወሀት ቡድን  ነው" ያሉት አቶ ተክለማርያም "በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው ህግ የማስከበር እርምጃ ከትግራይ ህዝብ ጋር ያለን ትስስር ያጠናክራል" ሲሉ ተናግረዋል ።

"የትግራይ ህዝብ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ በወንበዴው ቡድን ተጨቁኖ የኖረ ነፃ መውጣት የሚፈልግ ነው" ብለዋል ፡፡

አቶ አብርሀም ጨጋራ በበኩላቸው "ችግራችን ላለፉት 27 ዓመት ኢትዮጵያን በጉልበት ገዝተው ከቆዩና አሁንም በኃይል ወደ ሥልጣን እንመጣለን ብለው ከሚያስቡ በህወሀት ውስጥ ካሉ ጥቂት ግለሰቦች ጋር ነው" ብለዋል ፡፡

"ህግን የማስከበር ዘመቻው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሲጠናቀቅ የትግራይ ህዝብም ሆነ መላው ኢትዮጵያዊ ሠላም ያገኛል" ሲሉም ተናግረዋል።

"ከትግራይ ህዝብ ጋር አንድ ሆነን እንደኖርን ነገም አንድ ሆነን እንቀጥላለን" ያሉት ደግሞ አቶ እሰይ ሰራዊት ናቸው።

የትግራይ ህዝብ እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በሁሉም አካባቢ ካሉ ህዝቦች ጋር በወንድማማችነት የሚኖር እንደሆነ አስረድተዋል ፡፡

"በኛ መሀል የትግራይ ተወላጆችን እንደ ባዳ የሚቆጥር ነዋሪም ሆነ አመራር ካለ ራሱ የፅንፈኛውን አመለካከት የሚያራምድ እንደሆነ በመገንዘብ እንታገለዋለን" ብለዋል።

የጎፋ ዞን መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ድንበሩ ድርቤ በበኩላቸው መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ ህዝብ  ላይ ያነጣጠረ  በማስመሰል በማህበራዊ ትስስር ገፆች አሉባልታዎች እየተናፈሱ መሆኑን ተናግረዋል ።

አሉባልታዎቹ ቅሬታ እንዳይፈጥሩ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ከሌላው ህዝብ ጋር በፍቅርና በአንድነት እየኖሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም