ህግ የማስከበር እርምጃውን እንደግፋለን-በአዳማ የትግራይ ተወላጆች - ኢዜአ አማርኛ
ህግ የማስከበር እርምጃውን እንደግፋለን-በአዳማ የትግራይ ተወላጆች
አዳማ፣ ህዳር 13/2013 (ኢዜአ) መንግስት ህግ ለማስከበርና ሰላም ለማስፈን እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ በአዳማ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙ ትክክል መሆኑን አስተያየት ሰጭዎቹ ለኢዜአ አስታውቀዋል።
በከተማው ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች መካከል የገዳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ገብረእግዚአብሔር ኪዳኔ የትግራይ ህዝብ በክልሉ አፉ ተዘግቶ፣ተቆልፎና መንቀሳቀሻ አጥቶ የነበረ በመሆኑ ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙ ትክክል ነው ብለዋል።
"አሁን ላይ በክልሉ የህግ የበላይነትን እያስከበረ ያለው የመከላከያ ሰራዊትና ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሚሰጠው መመሪያ መሰረት ህብረተሰቡን ለማቋቋምና ለመርዳት ከጎኑ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።
"የክልሉን ህዝብ ከረሃብና ከውሃ ጥም ለማዳን በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ማገዝ ይገባቸዋል" ነው ያሉት ።
"ትግራይን መልሰን በማልማት ህዝቡን ከረሃብና ጭንቀት ማውጣት አለብን" ያሉት ነዋሪው በመከላከያና በመንግስት እየተወሰደ ያለው ህግን የማስከበር እርምጃን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
"የትግራይ ህዝብ የተጨቆነ በመሆኑ ፋታ የሚሰጠውን አካል ይፈልጋል" ብለዋል።
እየተወሰደ ያለው እርምጃ ህዝቡን ከረሃብ፣ከብዝበዛ፣ከጭቆናና ከአፈና የሚያላቅቅ በመሆኑ የተደሰቱበት እንደሆነ ገልጸዋል ።
"የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ መሰረት እንጂ ተነጥሎ የሚኖር አይደለም" ያሉት ደግሞ አቶ ገብረኪዳን ደስታ ናቸው።
"ሀገራችን እንዳትፈርስ፣ አንድነቷ ተጠብቆ በጋራ እንድንለማ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር አብረን እንሰራለን" ብለዋል።
በአዳማ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በክልሉ ሰላም እንዲሰፍንና ልማቱ እንዲቀጥል ከመንግስት ጎን ሆነው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል መከላከያ የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየወሰደ ያለውን እርምጃ አቅም በፈቀደ ሁሉ እንደግፋለን ብለዋል ።
ከሚኖሩበት አካባቢ ህብረተሰብ ጋር በመሆን ማንኛውንም አይነት እገዛ እያደረጉ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
ከጊዜያዊ አስተዳደርና አስተባባሪ ኮሚቴዎች ጋር በመሆን ክልሉን መልሶ የማቋቋም፣ ሰላምን ማስፈንና ልማቱ እንዲቀጥል ለትግራይ የሚያስፈልገውን ነገር እናደርጋለን" ሲሉም ተናግረዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩን ማቋቋምና ወደ ስራ ማስገባት ትክክልና አግባብ ነው፤ በግጭቱ የተፈናቀሉን ፈጥኖ መመለስና ማቋቋም ያስፈልጋል ብለዋል።
"ህወሃት ሁላችንም ባሳዘነ ሁኔታ ትልቅ ጥፋት ፈጽሟል፣ ህዝቡን በቀኝና በግራ ለረዥም ዓመታት የጠበቀው መከላከያ ላይ ክህደት ፈፅሟል" ያሉት ደግሞ በከተማው ቀበሌ 09 ነዋሪ ወይዘሮ ሲሳይ ሃይሌ ናቸው።
"በምሽግ ውስጥ ሆነውና ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ህዝቡን ሲጠብቁ የነበሩ የመከላከያ ሠራዊት ላይ በተፈፀመው ነገር በጣም አዝነናል" ብለዋል።
ህወሃት የጀመረው ጦርነት ራሱን እያጠፋ በመሆኑ ከመንግስትና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጎን በመሆን የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።