ቀጥታ፡

መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸው 19 ሐኪሞች አስመረቀ

ጎባ ህዳር 12/2013 (ኢዜአ)፡- መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ዶክትሬት የትምህርት ዘርፍ ያሰለጠናቸው 19 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው የዛሬ ተመራቂዎችን ጨምሮ 99 የህክምና ዶክተሮችን አሰልጥኖ አስመርቋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ዶክተር ጎይቶም ይስሃቅ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በቀሰሙት እውቀት ማህበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሀገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ የጤና ሁኔታ በመረዳት የሚሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው ተመራቂ ዶክተር ዮፍታኔ እንደሻው ናቸው፡፡

በዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጄይላን ቃሲም በበኩላቸው “ሆስፒታሉ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት በተጓዳኝ በተለያዩ የህክምና ሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል” ብልዋል።

ሆስፒታሉ የህክምና ዶክትሬት፣ አዋላጅ ነርስነትና ላብራቶሪ ቴክኒሻንነት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የጎባ ከተማ ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ ተመራቂዎች በተማሩት የጤና ሙያ ህዝቡን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል መንግስት መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እያደረገ የሚገኘውን ጥረት እንዲደግፉ አሳስበዋል።

የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋት በስሩ በሚገኘው የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል አማካይነት ህብረተሰቡን እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ሆስፒታሉ በህክምና ዘርፍ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ በዘርፉ የሚታየውን የሰው ኃይል እጥረት ለማቃለል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶክተር አህመድ ገለጻ፤ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ ከኮሮናቫይረስ ለመጠበቅ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባሻገር ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የመደገፍና ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

በ1999 ዓ.ም 742 ተማሪዎች ተቀብሎ ስራ የጀመረው መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ አሁን ላይ ከ24ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም