የዳውሮና ቤንች ሸኮ ዞኖች ለመከላከያ ሠራዊት 16 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አበረከቱ - ኢዜአ አማርኛ
የዳውሮና ቤንች ሸኮ ዞኖች ለመከላከያ ሠራዊት 16 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አበረከቱ
አዲስ አበባ ህዳር 12/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የዳውሮና ቤንች ሸኮ ዞኖች ለአገር መከላከያ ሠራዊት 16 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ።
የዞኖቹ ነዋሪዎች ለሠራዊቱ የላኩት ድጋፍ ጥሬ ገንዘብ፣ ሰንጋ በሬዎች፣ በግና ፍየሎች፣ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ማርና ቅቤ ይገኙበታል።
የቤንቺ ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አመን የዞኑ ሕዝብ ለአገር መከላከያ ሠራዊት በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጉንና ድጋፉም እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የዳውሮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ባንጉ በበኩላቸው ኅብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ያሰባሰበውን 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ጥሬ ገንዘብና የአይነት ድጋፍ ለአገር መከላከያ ሠራዊት መላኩን ተናግረዋል፡፡
የዞኑ ሕዝብ በቀጣይም ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመቆም ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ ለጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት በዞኖቹ ነዋሪዎች ስለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ድጋፉ ሠራዊቱ አገርና ሕዝብ ለማዳን እየፈጸመ ያለውን የጀግንነት ተግባር ከማገዝ ባለፈ የሞራል ስንቅ ይሆነዋል ብለዋል።
ከሁለቱም ዞኖች ተወክለው ድጋፉን ያስረከቡት የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ከሠራዊቱ የተቀነሱ ወታደሮችና ወጣቶች ሠራዊቱ ሕግ ለማስከበር እያደረገ ያለውን ተጋድሎ ለማገዝና ከጎኑ ለመቆም ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የህወሓት የጥፋት ቡድን በሠራዊቱ ላይ የፈጸመው ጥቃት በመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የተቃጣ እኩይ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።