ቀጥታ፡

ከድሬዳዋ እና ዲላ ዪኒቨርሲቲ ለሠራዊቱ ከ16ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

ድሬዳዋ/ዲላ/ ህዳር 12/2013( ኢዜአ) ከድሬዳዋ አስተዳደርና ዲላ ዪኒቨርሲቲ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚውል ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ እና ዓይነት ተለገሰ።

ከድጋፉ ውስጥ ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ከድሬዳዋ አስተዳደር ቀሪው ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ነው።

የድሬዳዋ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መብራቴ ገብረየስ ትናንት በተከናወነው የድጋፉ ስነ-ሥርዓት ወቅት እንዳሉት፤ የድሬዳዋ የገጠርና የከተማ ህዝብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ መሳካት በገንዘብ፣ እውቀትና ደም በመለገስ ድጋፉን እየሰጠ ይገኛል፡፡

በዕለቱ  ብቻ የከተማው ባለሃብቶች ከ13  ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ  ፣ የ38  ገጠር ቀበሌዎች ደግሞ አንድ ሚሊዮን 900ሺህ ብር   የሚገመቱ 35  የሐረር ስንጋዎችና ስምንት   ግመሎች መለገሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

እየተደረገ ያለው ድጋፍ  ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ከድጋፉ ውስጥ  የአሰሊሶ ገጠር ክላስተር ያበረከታቸውን አስር ሠንጋዎች  የኢፌድሪ አየር ኃይል የምስራቅ   ምድብ አዛዥ ኮረኔል አበበ ለገሰና የምስራቅ ዕዝ ተወካይ ሌተናል ኮረኔል ልጅአለም ምትኩ ተረክበዋል፡፡ 

ኮረኔል አበበ  በወቅቱ እንደገለጹት የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ የጀመረውን የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ተግባር በፍጥነት በማጠናቀቅ ውጤቱን ለመላው ዜጋ ይበሰራል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ ሀገርን ለመከፋፈልና ለማተራመስ ታጥቆ የተነሳው ከሀዲው ጁንታ በህግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል የተጀመረው  ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

በተመሳሳይ  ዲላ ዩኒቨርሲቱ  ለሠራዊቱ ያለውን አጋርነት ለመግለጽ የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን  የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶክተር ችሮታው አየለ  ለኢዜአ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ "ደማችንን ለመከላከያ ሠራዊታችን" መሪ ሀሳብ  የደም ልገሳ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ቀጣይነት ያለው  ድጋፍ ለማሰባሰብ እንደሚሰራም  ዶክተር ችሮታው አስታውቀዋል።

የዩኒቨርሲቲው መምህር አስናቀ እንድርያስ በሰጡት አስተያየት  የሀገር መከላከያ ሠራዊት እያከናወነ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም