የመንግስትን ህግን የማስከበር ስራ በመደገፍ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስትን ህግን የማስከበር ስራ በመደገፍ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ገለጹ
ሐረር ህዳር 12 /2013 (ኢዜአ ) ወንበዴው የህወሃት ቡድን ላይ መንግስት የተጀመረውን ህግ የማስከበር ስራ በመደገፍ አስፈላጊውን የህይወት መስዋትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን የምሥራቅ የቀድሞ መከላከያና ፖሊስ ሠራዊት አባላት ገለጹ።
አባላቱ እልህና ቁጭት በተቀላቀለበት የሀገር ፍቅር ስሜት ለኢዜአ እንዳሉት በተለይ በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመው ጥካኔ የተሞላበት ድርጊት ቡድኑን በጦር ወንጀለኝነት የሚያስከስሰው ነው።
በቀድሞው የሀገር መከላከያ 20ኛው ክፍለ ጦር የእግረኛ ሠራዊት አባል ሃምሳ አለቀ አለማየሁ ተሰማ በሰጡት አስተያየት ወንበዴው የህወሃት ቡድን በሰሜነ እዝ ላይ ያካሄዱት ግፍ የተሞላበት የጭካኔ ድርጊት የሚያንገበግብ መሆኑን ተናግረዋል።
ለራሱ ዓላማም ሲል ቀድሞ የነበረውን ሠራዊት የበታተነ እና ከጥንስሱ ጀምሮ የሀገሪቱን ህልውና ሲፈታተን የነበረ ወንበዴ ቡድን ነበር ብለዋል።
ሠራዊቱ ህግን ለማስከበር እየከፈለ የሚገኘውን መስዋትነት ለመጋራት ከጎን ለመሰለፍ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ሰሜን መሽጎ የሚገኘው የወንበዴ ቡድን በሰሜን እዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው ድርጊት እንደ ኢትዮዽያዊነቴ ከፍተኛ ቁጭት አሳድሮብኛል ያሉት ደግሞ የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የምስራቅ እዝ አባል የአስር አለቃ ይመኙሻል ተገኝ ናቸው።
በተለይ ወንበዴው የህውሃት ቡድን አለም አቀፍ ህግጋትን በመጣስ ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን በጦርነት እየማገደ መሆኑ እንዳሳዛናቸውና እንደሚያውግዙት ተናግረዋል።
በጦር ወንጀለኝነት እንዲጠየቅም የበኩሌን እወጣለሁ ብለዋል።
በቀድሞ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በምስራቅ ዕዝ የታንክና ብረት ለበስ መሳሪያ ሃላፊ ሻንበል ዳኛቸው አዱኛ ከሃዲው የህውሃት ቡድን በሰሜን እዝ ሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ እጅግ አሳዝኖኛል፤አስቆጥቶኛል፤በታሪክም በራስ ዜጋ ላይ የተፈጸመ ክህደት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከ30 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትኖ እንደፈለገ በአምባገነንነት የገዛ ከሃዲ ቡድን መሆኑን ጠቁመው በተለይ የኢትዮዽያ መከታ የሆነውን መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት የሚያሳዝንና የሚያስቆጣ ነው ብለዋል።
ይህንን እኩይ ተግባሩን ለመቀልስ መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ የቀድሞ ሠራዊትን በማሳተፍ ጭምር በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የመንግስት ጥሪ ሳንጠብቅ ዘምተን ሀገሪቱን ከከሃዲው ቡድን ለመታደግ ተዘጋጅተናልም ብለዋል።
ሌላው የቀድሞ ሠራዊት አባል የነበሩት መቶ አለቃ አንዳርጌ ካሴ በበኩላቸው ወንበዴው ጁንታ ኢትዮዽያን ለ40 ዓመታት ለችግር ያጋለጠና የቀድሞ ሠራዊትን ያፈረሰ ሀገር ጠል ቡድን መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ገበሬ እየሰራና እያረሰ ትምህርት ቤት እየገነባ ለነበረ ሠራዊት ታሪክ ይቅር የማይለውና የማይረሳው የጦር ወንጀል መፈጸሙ እንዳስቆጣቸው ገልጸዋል።
መንግስት ህግ እያስከበረ የሚገኘውን ተግባር በመደገፍ የሚያደርግላቸውን ጥሪ ተቀብለው ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።