የህወሓትን የክህደት ጥግ ለመመስከር የተረፈች ነፍስ - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓትን የክህደት ጥግ ለመመስከር የተረፈች ነፍስ
በአየለ ያረጋል(ኢዜአ)
ባለብዙ ሙያው ወታደር 'ወጥቶ አደር' የሆነው የሞቀ ቤት ሳይፈልግ ቀርቶ፣ የጣዕመ መና ሰልችቶችና ራሱን ጠልቶ አልነበረም። የጫማው ማሰሪያ ሳይፈታ ዋርድያ ላይ የተገተረው፣ ለዳር አገር ቃፊር የቆመው ለወገኑ ወግኖ ነው።
ለአገሩ ዳር ድንበር ጠበቃ፣ ለወገቡ ቤዛ ሲል ግምባሩን ለጥይት፣ ጀርባውን ለእናት አገሩ ለሚሰዋላት ከለላ ሆኖ ነው። ለሰንደቅ ዓላማው ክብር ከፍታ፣ ለአገሩ ሉዓላዊነት መከታ መሆንን መርጦ፣ በታነጸበት ወታደራዊ ምግባር ተገዶ ነው።
ከአንደበቱ እስከ ድርጊቱ በስነ ስርዓቱ ተመርቶ፣ ራሱን በራሱ መርቶ፣ መለዮውን አክብሮና አስከብሮ የሚኖር፣ ሕይወቱን በአገር ነጻነት ቀብድ አስይዞ የሚኖርበት ሙያም ነው።
ከድሮ እስከ ዘንድሮ ከአባቶች አርበኝነትን ተውሶ፣ ከአድዋ እስከ ምጽዋ ጀግንነትን ተላብሶ፣ ከኮሪያ እስከ ላይቤሪያ፣ ከኮንጎ እስከ ሶማሊያ፣ ዓለምን ባስደመመ ጀብዱ ኮርቶ፣ ጠላትን ድባቅ በመምታት ሰልቶ የኖረው የኢትዮጵያ ወታደር ወይንም ጦር ሰራዊት ደግሞ ይለያል።
ይህ ባለብዙ ገድል ወራሪን ድባቅ መምታት እንጂ ሌሎቹን በግፍ የመውረር ታሪክ የሌለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ግን በማይጠበቅ ቅጽበት፤ ጌታውን እንደሸጠው ይሁዳ በገዛ ወገኔ ተከዳ።
'የቅርብ ጠላቴን እንጂ የሩቁን እጠብቀዋለሁ' እንዲል አገሬውና ሠራዊቱ አገር አማን ብሎ በተኛበት በወዳጁ ጥቃት ተከፈተበት፤ ያጎረሰ እጁ ተነከሰ፤ የኖረበት ወታደራዊ ስነ ሰርዓትና ክብር የኔ ባላቸው ካሃዲያን ረከሰ።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 አመሻሽ ነው። ለሩብ ክፍለ ዘመን አገሩን በጠበቀበት፣ ወልዶ በከበደበት፣ ከማህበረሰቡ ተላምዶና ቤተሰብ መሰርቶ በቆየበት ሰፈር ሲጠብቀው የኖረውውን ቀዬ አገር አማን ብሎ ተኝቷል። ሰዓቱም ውደቅት ሆኗል፤ ልክ 5 ሰዓት ተኩል።
ትግራይ ክልል ኩይሃ ከተማ በሰሜን ዕዝ ውስጥ በሚገኘው አራተኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የእናቶች ሲቃ፣ የህጻናት ሰቆቃ ይሰማል።
በኢትዮጵያ መከላከያ አባልነት ለ32 ለዓመታት ያገለገሉት የክፍለ ጦሩ አመራር ሻለቃ አምሳሉ ደመቀ ለ20 ዓመታት በተቀመጡባት ኮይሃ ይህ ቀን ይመጣል ብለው ፍጹም አልጠበቁም ነበር። ግን ሆነ።
እናም 'ትረፊ ያላት ነፍስ' እንዲሉ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ የተቀመጡባትን ኩይሃን ለቀው ከአረመኔዎች መዳፍ አመልጠዋል።
ሻለቃ አምሳሉ "ከሃዲዎች ይህን ድርጊት ይፈጽሙብናል ብለን ባናስብም፤ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉና የሚሰሙ ነገሮች ነበሩ" ይላሉ።
በአገር ማንነት ጉዳይ አንዳች ልዩነት የማይንጸባረቅበትን ሠራዊት የፖለቲካ መጠቃሚያ ሲያደርግ የቆየው የህወሓት ቡድን ከ27 ዓመት በኋላ የመጣውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥም ሪፎርም መደረጉ እንዳልተስማማው ነው የሚናገሩት።
የሰራዊቱ አደረጃጀት ከአንድ ብሔር የበላይነት አመራር ተላቆ ሁሉን አሳታፊ በሆነ አግባብ በአዲስ መደራጀቱ ወታደሩን ያስደስት እንጂ ከህወሓት አንጃዎች ባሻገር በሰራዊቱ መዋቅር ያሉ ጥቂት የጦር አዛዦችና አመራሮችም እንዳልተደሰቱ ይናገራሉ።
በዚህም አንዳንድ የሠራዊቱ አመራሮች ጉዳዩን ብሔር ተኮር ዝንባሌ ከማድረግ ባለፈ የመንግስትን አቅጣጫ በመጣስ ጥቅሙ ተነክቶበት መቀሌ በመሸገው ዘራፊ የህወሓት ቡድን አመለካከት መጠለፋቸውንም ያምናሉ።
ለአብነትም እርሰቸው ባሉበት የ4ኛ ሜካናይዝድን ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ገብረስላሴ በላይን ጨምሮ በሰራዊቱ ውስጥ የሚገኙ አመራሮች ወታደራዊ የሪፎረም ስራውን ሲያስተጓጉሉ ከርመዋል።
ወታደራዊ ትጥቅ እንዳይሟላ የከባድ መሳሪያ መለዋወጫ ከወትሮው በተለየ እስከ አንድ ዓመት ማዘግየት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በሰራዊቱ ውስጥ በዘረጉት መዋቅር ከአንድ ዕዝ ወደ ሌላ ዕዝ የራሳቸውን ሰዎች ማዘዋወር፣ ሰራዊቱን በብሔር በማቧደን ለማወክና የእርስ በርስ ግጭት በመፍጠር የማፍረስ ሴራ ሲያሴሩ እንደነበር ያነሳሉ።
እነዚህ አመራሮች በሠራዊቱ ውስጥ ካሉ ኮሚቴዎች ጋር በጋራ ለመስራት ፈቃደኛ እንዳልነበሩ፣ ለሚቀርቡ ጥያቄዎችም 'እኔ ብቻ አውቃለሁ' በሚል እሳቤ ያለመቀበል በህሪያት ያንጸባርቁ ነበር።
ሻለቃ አምሳሉ ለማሳያነትም የትግራይ ክልል የራሱን ልዩ ኃይል ለማጠናከር በጡረታ የተገለሉ የመከላከያ ሠራዊቱ ጦር መኮንኖችን በክተት አዋጅ በመጥራት በክልሉ ልዩ ኃይል የመድፍ፣ የታንክ፣ የአየር መቃወሚያና ሌሎች ከባድ መሳሪያ ስልጠናዎች ሲያካሂድ እንደነበር ይገልጻሉ። ይህን ድርጊት ኮሎኔል ገብረስላሴ ቢያውቁም "መብታቸው ነው፤ ከቻሉ ከዚህ በላይ ቢያሰለጥኑ ምን አገባን" በሚል የሠራዊቱ አመራሮችን ስጋት ውድቅ ስለማድረጋቸውም ያስታውሳሉ።
ይህም አመራሮች ቀን ቀን ከሠራዊቱ ጋር ከአንገት በላይ እያወሩ፤ ማታ ማታ ግን መቀሌ ከመሸጉት የህወሓት የጥፋት ቡድን ጋር ልብ ለልብ ሲመሳጠሩና ሲያሴሩ እንደነበር ይገልጻሉ፤
በመጨረሻም የራሳቸውን ሰዎች በከባድ መሳሪያ አሰለጥነው ካበቁ በኋላ መሳሪያ ለመዝረፍ ወደ አገር መከላከያ ሠራዊቱ መምጣታቸውን ይገልጻሉ። ይህን ያደረጉትም ከተራ አባል አስከ ክፍለ ጦር አዛዠ ወገን ለይተው በመመሳጠር ለሩብ ክፍለ ዘመን አብሯቸው በነበረ፣ በበላና በጠጣ ሠራዊት ላይ ከሃዲነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ያነሳሉ።
ሻለቃ አምሳሉ የጥቃቱን ሂደትም ይተርካሉ። ጥቅምት 24 ሌሊት አገር አማን ብሎ በተኛ የመከላከ ሠራዊት ላይ ጥቃት ለመፈጸም በቅድሚያ ካሃዲ አዛዦች ለዋርድያ (ለዕለቱ ተረኛ ዘብ) ብቻ ይበቃል በሚል የሠራዊቱን መሳሪያ ወደመጋዘን እንዲጠረነፍ ማድረጋቸውን ያነሳሉ።
ጥቃቱን የፈጸሙት በሠራዊቱ ጋር ለዓመታት በኖሩ የራሳቸውን ሰዎች በማደራጀት፣ የትና በማን እጅ መሳሪያ እንዳለ የሚጠቁሙ የውስጥ አባላትን በሙሉ ወደራሳቸው ወገን በማድረግ ጭምር ነው።
ሠራዊቱ ወስጥ በተለያዩ ሙያዎች ( ከሾፌር አስከ ጋራዠ ሠራተኞች) በመመልመል ለክልሉ ልዩ ኃይል እንዲያመላልሱ ተደርጓል። ጥቃት ሲጀመር ወታደሩ ወደ መጋዘን ሄዶ መሳሪያ እንዳያነሳ ዙሪያውን በክልሉ ልዩ ኃይል እንዲከበብ አድርገዋል። ከዛም የመገናኛ እና ዋርድያዎችን በቅድሚያ ገድለዋል።
ከሃዲዎች በካምፕ ውስጥ የሚገኙ ከቀላል እስከ ከባድ መሳሪያ መጫን ጀምረዋል። ከዛም ሆነ ተብሎ ትጥቁን እንዳይዝ ያልተደረገውን ሠራዊት ከ400 በላይ ሰው መያዝ በሚችል አዳራሽ እንዲገባ ትዕዛዝ ተላለፈ። በድርጊቱ ያልተስማሙትንም ከዋርድያ እስከ መገናኛ ባለሙያዎች ተገድለዋል። ወደ ጦር መጋዝኑ የሚሄዱትንም ቀድመው ባስቀመጧቸው ልዩ ኃይሎች እንዲገደሉ ተደረጉ። ሠራዊቱም ሁለት አማራጭ ቀረበለት-አንድ ከካሃዲው ወገን ሆኖ መንግስትን እንዲወጋ፤ ሁለት በራሱ ሕይወት እንዲፈርድ።
ሠራዊቱ በስፍራው በቆየባቸው ዓመታት ከትግራይ ህዝብ ጋር በፍቅር መኖሩን፣ ህዝቡን ከጠላት የሚጠብቀው እንዲሁም ከደመወዙ ቀንሶ የሚያግዘውና አንበጣ የሚከላከልለት ሰራዊት መሆኑ ይገልጻሉ።
ድርጊቱን የፈጸሙት ግን በአንድ ሠራዊት ውስጥ ሆነው በብሔር አመለካከት የተዘፈቁ መኮንኖች ጥቅማቸው ከተነካባቸው የህወሓት ሰዎች ጋር በመመሳጠር መሆኑን ይናገራሉ።
ለውጡን ያልተቀበለው የህወሓት የጥፋት ቡድን ህዝቡን ከሠራዊቱ ለመነጠል ያልሰሩት ሴራ እንዳልነበር ገልጸው፤ ዳሩ ወጣቱ 'ቀድሞ አንድ ዳቦ ሳታቀርቡልን ከፌዴራል መንግስት ጋር ስትጣሉ እኛን ወደ ጦርነት ለማስገባት ፈልጋችኋል' በሚል እንዳልተቀበለቸው ይናገራሉ።
ለዚህ አብነትም የካሃዲው ቡድን ቀንደኛ አባል የሆኑት አቶ ስዩም መስፍን በኩይሃ ወጣቶችን ሰብስበው ቅስቀሳ ባደረጉብት ወቅት ወጣቱ ሰብሰባ ረግጦ በመውጣት እንዳዋረዳቸው ያስታውሳሉ።
ህወሓት ያደራጀው ልዩ ኃይልም ከፍተኛ አፈና በመፈጸም የትግራን ህዝብ ሲያስመርር እንደነበር የተቃወሙትንም ለእስር ሲዳርግ እንደነበር ያነሳሉ።
የህወሓት ሰዎች ሲቪል ሰዎችን በመላክ በከተማ የሚንቀሳቀሱ የሠራዊቱ አባላት ማንነት ተኮር ስድብ በመሰደብ፣ አንዳንዴም ድብደባ ሁሉ እንዲፈጸም በማድረግ፣ ሰራዊቱም ወደ ሌላ ነገርና ትንኮሳዎች እንዲገባ ጥረዋል። ሠራዊቱ ግን በትግስት ሁሉንም ማክሸፉን ነው ያስታወሱት።
ይህ አልሳካ ሲላቸው በመጨረሻ ራሳቸው በመግባት ጦር ሠራዊቱ ላይ በክህደት ጥቃት እንደፈጸሙበት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሠራዊት በማንም ጠላት ተደፍሮ እንደማያውቅ የሚገልጹት ሻለቃ አምሳሉ፣ በዚህ አሳፋሪ ክህደት ክፉኛ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
ለመሆኑ ሻለቃ አምሳሉ ደመቀ ከጥቃቱ እንዴት ተረፉ?
መሳሪያውን ዘርፈው ጀሌውን ያስቀመጡትን ሰራዊት ሰብስበው የራሱን ወገን እንዲወጋ ሲወስኑ ማምለጣቸውን ይገልጻሉ። አዲ ጉደም ከተባለች ስፍራም መኪና አግኝተው እስከ አላማጣ መጥተዋል። በተካዱበት ክልል በማሽላ አዝመራ ውስጥ ተሽሎክሉከው ቆቦ በመግባት ሕይወታቸውን አትርፈዋል።
"የመከላከያ ሠራዊታችንን ፊት ለፊት ማንም ገጥሞት አይመልሰውም፣ በጀግንነቱ እተማመናለሁ" የሚሉት ሻለቃ አምሳሉ፤ እንደ ጀግና ፊት ለፊት መግጠም የማይችሉ ሴረኞች የፈሪ ጥቃት እንደፈጸሙበት ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ በሚያምነውና በግዳጅ አፈጻጽሙ በሚያኮራው ሠራዊቱ ላይ የተፈጸመበት የክህደት ጥቃት እንዳስቆጣቸው በመግለጽ፤ በዚህም ህዝብን ከዳር እስከ ዳር በማነቃነቅ በወኔና በቁጭት መነሳቱን አድንቀዋል።
በድርጊቱ የተቆጩት ሻለቃ አምሳሉ በሰሜን ዕዝ የተለዩዋቸው ጓዶቻቸው ዕጣ ፈንታ አሳስቧቸዋል። በማንኛውም ግዳጅ በወኔና በእልህ በመሰማራት የጓዶቻቸውን ጠላቶች ለመበቀል ዝግጁ ናቸው። አሁን ላይ በመንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ የሚያኮራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
እርምጃው ውጤታማ እንዲሆንም የኢትየጵያ ህዝብ በወኔና በቁጭት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ሻለቃ አምሳሉ ጥሪ አቅርበዋል።