ቀጥታ፡

የአገር መከላከያ ሠራዊትን መደገፍ ኢትዮጵያን መደገፍ ነው - አቶ ዣንጥራር አባይ

አዲስ አበባ ህዳር 12/2013 (ኢዜአ) የመከላከያ ሠራዊቱ እየተወጣ ያለውን ሕግና የአገር ሕልውና የማስከበር ሃላፊነት መደገፍ ኢትዮጵያን መደገፍ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር ዓባይ ገለፁ። 

አቶ ዣንጥራር የአዲስ አበባ የካና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊት ያበረከቱትን የ91 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ባስረከቡበት መርሃ ግብር ነው።   

ከነዋሪዎቹ የተበረከተውን 73 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ፣ 145 ሰንጋዎች፣ 175 በግና ፍየል እንዲሁም ምግብ ነክ ድጋፎች ለመከላከያ ሠራዊት አስረክበዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱን መደገፍ ኢትዮጵያን መደገፍ ነው ያሉት አቶ ዣንጥራር ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለው የደም ልገሳ፣ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸዋል።

መከላከያ ሠራዊቱ መስዋዕትነት እየከፈለ አገር እየጠበቀ መሆኑን ገልጸው ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ኩራት የሆነው ኃይል ክብርና ምስጋና ይገባዋል ነው ያሉት።  

ለሠራዊቱ የሚደረገው ድጋፍ የልማት አካል ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ተክሌም ጀግኖች እናትና አባቶች መስዋዕትነት ከፍለው ያቆዩልንን አገር እኛም የሚጠበቅብንን ተወጥተን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ብለዋል።  

በሠራዊቱ ላይ የተፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት መላ ኢትዮጵያዊያንን ማስቆጣቱን በመግለፅ የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ካላፈረሰ የማይተኛ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል ሲሉ ተናግረዋል።   

በሴራ የተሞላውና ሕዝቡን ከፋፍሎ ሲያባላ የቆየው ቡድኑ ግብዓተ መሬቱ እስኪፈጸም ደረስ ሕዝቡ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ሙሉ ሞጎስ ሠራዊቱ እየወሰደ ባለው እርምጃ ድል እያደረገ መሆኑን ገልፀው ድጋፉ ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆነዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም